ቀጥታ፡

በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሂደት ያጋጠሙ እንከኖች በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ተገለጸ

ኢዜአ ህዳር 10/ 2012  በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሂደት አንዳንድ ያጋጠሙ እንከኖች በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር በኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት ጊዜያዊ ኮሚቴ ገለጸ ፡፡

ኮሚቴው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ሰላማዊ ሆኖ እየቀጠለ ቢሆንም የታዛቢና የቁሳቁስ እጥረት እንደገጠሙት አስታውቋል።

''እጥረቱ በውጤቱ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ'' የለም ብሏል።

ኮሚቴው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫ አስፈፃሚዎች የተሟሉ ቢሆንም በአንዳንድ ጣቢያዎች ከተፈቀደው ሰአት ቀድመውና ዘግይተው በመከፈታቸው የምርጫ ቁሳቁሶች ርክክቡን ታዛቢዎቹ ማዬት አልቻሉም።

ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይም የአንድ ወገን ተወካዮች ብቻ መገኘታቸውንና አንዳንዶቹ ላይም አንድ አይነት ምልክት ብቻ የያዘ ባነር የተሰቀለበትም መኖሩን የኮሚቴው ቡድን መሪ ወይዘሮ ብሌን አስራት በመግለጫው ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የህዝብ ብዛትና መጨናነቅ በመኖሩ የመስተጓጎል አዝማሚያ መታየቱን ኮሚቴው አመልክቷል።

የሲቪክ ማህበራት ኮሚቴው በሲዳማ ዞን 24ቱም ወረዳዎች ላይ ታዛቢዎች ያሰማራ መሆኑንና የተፈጠሩት ችግሮችም በውጤቱ ላይ ተጽዕኖ ያመጣሉ ብሎ እንደማያምን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ወይዘሮ ሶሊያና ሽመልስ በበኩላቸው ከተፈቀደው ጊዜ በፊትና ዘግይተው የተከፈቱ ምርጫ ጣቢያዎች መኖር አለመኖሩን በተመለከተ የደረሳቸው መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል።

''ደረሰ በተባለው ችግር ግን የተስተጓጎለ አንድም ምርጫ ጣቢያ የለም'' ብለዋል።

''ይሁን እንጂ የአንድ ወገን ጫና ከማድረግ አኳያ በአንዳንድ አካባቢዎች ከስራ አስፈፃሚዎቹ ውጭ ለመራጮች ግንዛቤ ይሰጣሉ የሚል መረጃ ደርሶን የእርምት አርምጃ እንዲወሰድ አድርገናል'' ብለዋል።

የቁሳቁስ እጥረት አለመግጠሙንም የቦርዱ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ ወይዘሮ ሶሊያና ተናግረዋል።

የታዛቢዎቹን በተመለከተ የጎጆ ምልክትን የሚወክሉ ሰዎች የደቡብ ክልል እንዲልክ ተጠይቆ በሚጠበቀው ልክ ባለመላኩ አንዳንድ ቦታዎች የሻፌታ ምልክት ተወካዮች ብቻ ያሉባቸው ጣቢያዎች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።

እስካሁን ያለው የምርጫ ሂደት ሰላማዊ ሆኖ እየቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም