የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ ይገኛል

69
ህዳር 10/2012 የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ሰላማዊና ነፃ ሆኖ መቀጠሉን ታዛቢዎችና መራጮች ተናገሩ። የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ በሰላማዊ መንገድ እየተከናወነ እንደሚገኝ በስፍራው የሚገኘው ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው መራጮችና ታዛቢዎች ገልጸዋል። ኢዜአ ከአዋሳ እስከ ይርጋለም ከተማ ያሉ የምርጫ ጣቢያዎችን ተዘዋውሮ የምርጫ ሂደቱን ለመቃኘት  ሞክሯል። በአካባቢዎቹ የተዘዋወረው ሪፖርተራችን ያነጋገራቸው መራጮችና ታዛቢዎች እንዳሉት የምርጫው ሂደት ሰላማዊ ፣ዴሞክራሲያዊና ህዝቡ በነጻነት እየተሳተፈበት የሚገኝ ነው። ከመራጮች አንዱ የሆነት ኦካ ቦቻ እንዳሉት በሌሊት በስፍራው መገኘታቸውን ገልጸዋል። አብዛኛው መራጭም በአሁኑ ሰዓት በሰላም መርጦ እየተመለሰ ይገኛል። የምርጫ አስፈፃሚዎችም ለመራጮች የምርጫ ሂደቱን የማስረዳትና የማስገንዘብ ስራ እየሰሩ መሆኑን  ገልጸዋል። ሌላኛዋ መራጭ ወይዘሮ ታየች ታምራት ያለማንም ጫና በነፃነት የሚፈልጉትን መርጠው መመለሳቸውን ተናግረዋል። የምርጫ ታዛቢ አቶ ዮሴፍ ፅጌ በበኩላቸው ሁሉም የምርጫ ቁሳቁሶች ተሟልተው ርክክብ ከተደረገ በኋላ ሰዓቱን ጠብቆ 12 ሰዓት ላይ መጀመሩን ተናግረዋል። የምድረ ገነት ምርጫ ጣቢያ ቁጥር ሁለት የህዝብ ተወካይና የምርጫ ታዛቢ የሆኑት አቶ ሲዳሞ ቦንሴ    በበኩላቸው የህዝበ ውሳኔ ምርጫው ህግን በተከተለ መልኩ እየተከናወነ ነው ብለዋል። በእስካሁኑ ሂደት ምንም አይነት የሰላም ሆነ የፍትሃዊነት ችግር አልታየም ነው ያሉት።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም