ቀጥታ፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስራ መሳተፍ ታሪካዊ አሻራ ማሳረፍ ነው - የግድቡ ኢንጂነሮች

ኢዜአ ህዳር 10/2012   የሕዝብ ፕሮጀክት በሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስራ መሳተፍ ታሪካዊ አሻራ ማሳረፍ መሆኑን በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ገለጹ። ሠራተኞቹ በሕዳሴ ግድቡ በሚያከናውኑት ስራ ታላቅ ደስታና ኩራት እንደሚሰማቸውም ተናግረዋል። ኢዜአ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከተጀመረበት 2004 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሙያ መስኮች በመስራት ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን አነጋግሯል። በሕዳሴ ግድቡ በከፍተኛ ላቦራቶሪ ቴክኒሺያንነት እያገለገሉ ያሉት ኢንጂነር ውብሸት አባይ ከቤተሰብ መለየት ከባድ ቢሆንም ስራው ከአገር የተሰጠ ትልቅ አደራ በመሆኑ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል። ባለሙያዎቹ በሕዳሴ ግድቡ የተገኙት ኢትዮጵያን ሌሎች ከደረሱበት የዕድገት ደረጃ ለማድረስ እንደሆነና ለዚህም በቁርጠኝነት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል። ኢንጂነር አውራሪስ ታፈሰ በ2003 ዓ.ም ለሕዳሴ ግድቡ የቁፋሮና ቦታ የመለየት ስራ ሲጀመር ጀምሮ የነበሩ ሲሆኑ በዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ተቆጣጣሪነት በመስራት ላይ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ሕዝብ በሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ አገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት አሻራቸውን ለማሳረፍ እስከ ፍጻሜው በትጋት እንደሚሰሩም ነው የገለጹት። ከልጆቻቸውና ከቤተባቸው ቢርቁም ዋናው ቁም ነገር ስራን ማክበር ከምንም በላይ ደግሞ አገራዊ ግዴታን መወጣት እንደሆነም አክለዋል። በግልገል ጊቤ 1፣ 2 እና 3 የኃይል ማመንጫ በከፍተኛ የፕሮጀክት ዲዛይን ስራ ተሳትፈዋል፤ በሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም በዚሁ ሙያ እየሰሩ ነው ኢንጂነር ፈቃዱ ተክሌ። ቀደም ሲል የሰሩባቸውን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ፕሮጀክት ብለው እንደሚጠሯቸው፤ የሕዳሴ ግድብን ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፕሮጀክት እንደሆነ ይናገራሉ። 'ጫና ቢኖረውም ስራችንን የምንሰራው ደስተኞች ሆነን ነው' ይላሉ ኢንጂነር ፈቃዱ። ቤተሰባቸው ድጋፍ እንደሚያደርግላቸውና በግድቡ ስራ መሳተፍም ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት በመሆኑ ስራቸውን በዛ መንፈስ እንደሚያከናውኑ ነው የገለጹት። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ከፍተኛ የላቦራቶሪ ቴክኒሺያን ኢንጂነር ሽፈራው ዳምጤም እስከ ግድቡ ፍጻሜ በመስራት የተረከቡትን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ይገልጻሉ። የሕዳሴ ግድቡ ስራ ቆሟል የሚባለው ትክክል እንዳልሆነ፤ ባለሙያውም የዕለት ተዕለት ስራውን እየከወነ በመሆኑ በዓይን የሚታዩ ተጨባጭ ለውጦች መኖራቸውን ተናግረዋል። ከሚወራው ይልቅ በአካል ተገኝቶ እየተሰራ ያለውን መመልከት ግድቡ ያለበትን ደረጃ ለማወቅ ያስችላል ነው ያሉት ባለሙያዎቹ። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 69 ነጥብ 37 በመቶ ደርሷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም