የድህረ ምርት ብክነትን የሚቀስን "ዜሮ ፍላይ" የተሰኘ የእህል ማከማቻ ከረጢት ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድህረ ምርት ብክነትን የሚቀስን "ዜሮ ፍላይ" የተሰኘ የእህል ማከማቻ ከረጢት ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ነው
ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2012 የድህረ ምርት ብክነትን የሚቀንስ በኬሚካል የታከመ "ዜሮ ፍላይ" የተሰኘ የእህል ማከማቻ ከረጢት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን የፌዴራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ገለጸ። ቴክኖሎጂውን ለባለድርሻ አካላት የሚያስተዋውቅ የምክክር መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የኤጀንሲው የሕብረት ሥራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው እንደገለጹት ኤጀንሲው የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ ይገኛል።
ቀደም ሲልም የድህረ ምርት ብክነትን ሊቀንሱ የሚችሉ ውጤታማ የእህል ማከማቻ ከረጢቶችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት የምርት ብክነትን ለመከላከል ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በኬሚካል የታከመ "ዜሮ ፍላይ" የእህል ማከማቻ ከረጢት እስከ ሦስት ዓመት በተባይ ሳይጠቃ ጠብቆ ማቆየት እንደሚችልም ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው እንደሀገር የሚደርሰውን የድህረ ምርት ብክነት የመቀነስ አቅሙ ከፍተኛ መሆኑ በጥራት ተቆጣጣሪ ድርጅቶችና በአለም ምግብ ድርጅት መረጋገጡን ዳይሬክተሯ አስረድተዋል።
ከረጢቱ ነቀዝና ሌሎች ተባዮችን የመከላከል አቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት ከአስመጭው ኩባንያው ጋር የጋራ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል።
በተደረሰው ስምምነት መሰረትም በአሁኑ ወቅት በ20 የሕብረት ሥራ ማበራት በኩል ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እየተሰራጨ መሆኑን አመልክተዋል።
"ይህም የሕብረት ሥራ ማህበራት በምርት ግብይት ወቅት ጥራት ያለው ምርት ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ አገሪቱም ሆነች አርሶ አደሩ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል" ብለዋል።
የ"ዕድሜ ዓለም እጅጉ ቢዝነስ ግሩፕ" ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ እድሜዓለም እጅጉ በበኩላቸው በድህረ ምርት ወቅት እስከ 30 በመቶ የሚደርሰው የምርት ብክነት መቀነስ ቴክኖሎጂውን ከውጭ አገር ለማስገባት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመትም ለመጀመሪያ ጊዜ 5 ሚሊዮን በኬሚካል የተነከረ ዜሮ ፍላይ የእህል ማከማቻ ከረጢቶችን በማስመጣት ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ሥራ አስኪያጁ አንዳሉት ለአርሶ አደሩ እየተሰራጨ ያለው ከረጢት 50 እና 100 ኪሎ ግራም እህል መያዝ የሚችሉ ሲሆን ዋጋቸውም 18 እና 23 ብር ነው።
ከረጢቱን በቀጣይ በአገር ውስጥ ለማምረት ድርጅታቸው በ1 ቢሊዮን ብር ወጭ በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የከረጢት ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት መሬት ተረክቦ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተገንብተው የሚጠናቀቁት ፋብሪካዎችም በቀን 500 ሺህ በኬሚካል የተነከሩ የእህል ማከማቻ ከረጢቶችን በማምረት ለአገር ውስጥና ለአፍሪካ ገበያ ምርት ማቅረብ የሚችሉ ናቸው።
ምርት ከተሰበሰበ በኋላ በአያያዝ ጉድለት በተለያዩ ተባዮች እንደሚጠቃና የምርት ብክነት እንደሚከሰት የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ናቸው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለውን ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱ የነበረውን የምርት ብክነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚያስችል አስረድተዋል።
በተለይም በተባይ ፈጥነው የሚጠቁ የጥራጥሬ፣ የአገዳና የቅባት እህሎችን በከረጢቱ ቅድሚያ ሰጥቶ በማስቀመጥ የሚስተዋለውን የምርት ጥራትና ብክነት ችግር በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ገልጸዋል።
የፀሐይ ዩኒየን የግብይት ባለሙያና የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሪት አለምፀሐይ አህመድ በሰጡት አስተያየት ቴክኖሎጂው ካለው ጥቅም አኳያ በብዛትና በፍጥነት ለአርሶ አደሩ እንዲቀርብ ጠይቀዋል።
"የዩኒየኑም ሆነ የአባል አርሶ አደሮች ችግር አንድን ምርት ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ በማቆየት በኩል ያለው ውሱንናት ነው" ያሉት ባለሙያዋ፣ ቴክኖሎጅው ችግሩን በዘላቂነት እንደሚፈታላቸው ግንዛቤ በመድረኩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ከክልሉና ከፌደራል ሕብረት ሥራ ማህበራት፣ ከዩኒየኖችና ከግብርና ቢሮ የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።