ኢትዮጵያ ከዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታጠናክር ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታጠናክር ተገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 ኢትዮጵያ ከዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታጠናክር ተገለጸ። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ አምባሳደር ሆነው ከተሾሙት አምባሳደር ጅን ሊዮን ሊጋንዱ የሹመት ደብዳቤ ኮፒ ዛሬ በተቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር "ኢትዮጵያ ከዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ አጠናክራ ትቀጥላለች" ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኙ አምስት ከተሞች በሳምንት 22 ጊዜ በረራ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያሳድገው መናገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ለሚያከናውኑት ስራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጎናቸው የማይለይ መሆኑን ገልጸውላቸዋል። አምባሳደር ጅን ሊዮን ሊጋንዱ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ለ10 ዓመታት ያክል በተለያዩ የስራ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ መኖራቸውን አስታውሰው፤ "ከቤቴ እንደመጣሁ ነው የምቆጥረው፣ የአፍሪካ መዲና ከሆነችው ኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ለመስራት በመምጣቴ በጣም ደስተኛ ነኝ" ብለዋል። አምባሳደሩ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1960 በዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ የነበረውን ግጭት ለማስቆም የሰላም አስከባሪ ሃይል መላኳን የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውሷል። በሌላ ዜና የኢትዮጵያና የህንድ 70ኛ አመት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በህንድ ርዕሰ መዲና ኒውደልሂ ተከበሯል። በህንድ የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አስፋው ዴንጋሞ፤ ላለፉት 70 ዓመታት የሁለቱ አገሮች የንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታ፣ እንዲሁም የትምህርት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ውጤታማ እንደነበር ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በአገራችን ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የህንዱ ፕሬዝዳንት ራም ናት ኮቪንድ እንዲሁም በያዝነው ዓመት ግንቦት ላይ በህንድ ጉብኝት ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ያደረጓቸው ጉብኝቶች "የአገሮቹን የግንኙነቱን ጥንካሬ ያሳያል" ብለዋል፡፡ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣት የህንድ ባለሃብቶች በአገራችን የሚያፈሱት መዋዕለ ንዋይ እንዲጨምር ማድረጉን አምባሳደሩ ተናግረዋል። የህንድ ባለሃብቶች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና ምርቶች ማቀነባበር፣ በማኑፋክቸሪንግ እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው በብዙ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን የስራ እድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል። በህንድ የቴክስታይል ሚኒስትር ሽሪ አጃይ ታምታ በበኩላቸው በቅርቡ በተደረገው ሁለተኛው የኢትዮ ህንድ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ "የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የጋራ መግባባት መፈጠሩን በመጠቆም "ለተግባራዊነቱ ተግተን እንሰራለን" ብለዋል።