በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ህንጻ ላይ የተነሳ እሳት የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አንድ ህንጻ ላይ የተነሳ እሳት የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር ዋለ
ኢዜአ ህዳር 9/2012 በጎንደር ዩንቨርሲቲ ቴዎድሮስ ካምፓስ የተማሪዎች የማደሪያ ህንጻ ላይ ዛሬ ምሳ ሰአት ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ስር መዋሉን ዩንቨርሲቲው አስታወቀ። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንቱ ዶክተር አስራት አጸደወይን ለኢዜአ እንደተናገሩት የእሳት አደጋው የደረሰው የ1ኛ ተማሪዎች የሚገለገሉበት T-35 የተባለው የማደሪያ ህንጻ የመጨረሻ ፎቅ ላይ ነው፡፡ ቃጠሎውን ለመቆጣጠርም የከተማውና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የእሳት አደጋ ተሸከርካሪዎች ፈጥነው በመድረስ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የዩንቨርሰቲው ማህበረሰብ አባላትና ተማሪዎች የጸጥታ ሃይሉና የከተማው አመራሮች እሳቱን ለመቆጣጠር ያደረገው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል። በቃጠሎው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የተናገሩት ፕሬዘዳንቱ በንብረት ላይ መጠነኛ ጉዳት ከማድረስ ውጪ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡ የቃጠሎው መንስኤ እስከ አሁን በውል እንዳልታወቀና የከተማው ፖሊስም በስፍራው ተገኝቶ የማጣራት ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በዩኒቨርሲቲው ጥቂት የትምህርት ክፍሎች ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር በዚህ ሳምንት ሙሉ በሙሉ መጀመሩንም ፕሬዘዳንቱ አስታውቀዋል፡፡