የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን በማስፋት የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተገለጸ

245

ኅዳር 09 ቀን 2012 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን ተደራሽነት በማስፋትና ጥራቱን የጠበቀ ስልጠና በመስጠት የስራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተገለጸ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን  ለማሳደግና ውጤታማ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች  ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር እያደረጉ ነው።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብዲዋሳ አብዱላሂ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በዓለም የበለጸጉ አገሮች ቴክኒክና ሙያ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ቴክኖሎጂን በመጠቀማቸው ነው።

በመሆኑም ከድህንነት ለመውጣት ለወጣቶች የስራ እድል አጥነትን ለመፍታትና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተለይም የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት ፍትሐዊ የተደራሽነት ችግርና ጥራት ያለው የስልጠና ጉድለት የዘርፉ ከፍተኛ ማነቆዎች በመሆናቸው በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ይህንኑ ለመፍታትም ስልጠናው ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጀምሮ እንዲሰጥ በአዲሱ ትምህርት ፍኖተ ካርታ መካተቱን ጠቁመዋል።

በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና የሚወስዱ ሰልጣኞች ዝቅተኛ ነጥብ ያላቸው ተማሪዎች በመሆናቸው የጥራት ጉድለት እንደምክንያት ከሚነሱ ጉዳዮች ይጠቀሳል።

ዝቅተኛ ነጥብ ያላቸው ተማሪዎች ወደዚሁ ዘርፍ መግባት የትምህርትና ስልጠና ጥራት ችግር እንዱ ምክንያት መሆኑን የገለጹት ዶክተር አብዲዋሳ፤ በመሆኑም ይህንኑን ችግር ለመፍታት ወደዚሁ ዘርፍ የሚገቡ ተማሪዎች በፍላጎታቸውና ወደ ዩኒቨርሲቲዎች በሚገቡበት ውጤት ደረጃ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ወደዚሁ የስልጠና ዘርፍ የሚገቡ ተማሪዎችን ደካማ አድርጎ ማሰብ ትክክል ባለመሆኑ ይህ እሳቤ እንዲለወጥ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል።

''የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠናን ውጤታማ ለማድረግ የግል ዘርፉን ማሳተፍ ይጠበቅበታል ያሉት'' ዶክተር አብዲዋሳ፤ እስካሁን የግሉ ዘርፍ በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና አለመሳተፉ አንድ ተግዳሮት እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም ከመንግስት በተጨማሪ የግል ባለሃብቶች በዘርፉ የበኩላቸን እንዲወጣ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የውይይት መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት አቶ ኃይለሚካኤል አስራት በበኩላቸው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ጥራት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በተለይም ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ለዘርፉ ውጤታማነት የላቀ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

ተመርቀው የሚወጡ ሙያተኞችን ከኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር ገበያ ተኮር ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ማስቻል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እያታየ ያለው አለመረጋጋት እንዱ ምክንያት ስራ አጥነት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይለሚካኤል፤ ዘርፉን በማሳደግ የወጣቶችን የስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም