የሶስትዮሽ ውይይቱ በሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ አያሳድርም - ኢንጂነር በላቸው ካሳ

52
ኢዜአ  ህዳር 9/2012  በአሜሪካ የተካሄደው የሶስትዮሽ ውይይት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የስራ እንቅስቃሴ ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ እንደሌለውና ስራዎች በአግባቡ እየተከናወኑ መሆናቸውን በምክትል ፕሮጀክት ማናጀር ማዕረግ የሕዳሴ ግድቡ ፕሮጀከት ሳይት አስተባባሪ ኢንጂነር በላቸው ካሳ ገለጹ። ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም በአሜሪካ ጋባዥነት የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸው የሚታወስ ነው። ከውይይቱ በኋላም አገራቱ ተቋርጦ የነበረውን የሶስትዮሽ የቴክኒክ ስብስባ ለመጀመር የተስማሙ ሲሆን የመጀመሪያው የቴክኒክ ስብሰባ ህዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በምክትል ፕሮጀክት ማናጀር ማዕረግ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሳይት አስተባባሪ ኢንጂነር በላቸው ካሳ የአሜሪካው የሶስትዮሽ ውይይት በግድቡ ስራ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንደሌለና ስራዎች በሚያስፈልገው ፍጥነት እየተከናወነ ነው ብለዋል። በአሜሪካ የተካሄደው ውይይት በቴክኒክ ደረጃ ተቋርጦ የነበረውን ውይይት ያስጀመረና በግድቡ ዙሪያ ለሚነሱ ጉዳዮች በፍጥነት እልባት ከመስጠት አንጻር የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ማንንም አገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላትና የሚካሄዱት ውይይቶችም ጉዳዮች በቶሎ እንዲቋጩ ያደርጋል ብለው እንደሚያምኑም ኢንጂነር በላቸው ገልጸዋል። ኢዜአ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እንቅስቃሴን የተመለከተ ሲሆን የግንባታ ስራው ቀንና ምሽትም ሳይቋረጥ እየተከናወነ መሆኑን ለማየት ችሏል። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 69 ነጥብ 37 በመቶ የደረሰ ሲሆን በጣልያኑ የግንባታ ተቋራጭ ሳሊኒ ኢምፔር ጂሎ የሚከናወነው የሲቪል ምህንድስና ስራ 85 በመቶ ተከናውኗል። በብርታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ተይዘው የነበሩ ስራዎች የስቲል ስትራክቸርና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ለስድስት የውጭ አገራት ተቋራጮች መሰጠታቸው ይታወቃል። የስቲል ስትራክቸር ስራው ከ15 በመቶ በላይ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራው ደግሞ 29 በመቶ ተከናውኗል። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በ2015 ዓ.ም ለማጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለታል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም