ብልጽግና ፓርቲ ብልጽግናን በሁለንተናዊ አግባብ የሚያረጋግጥ ነው --ዶክተር አብይ አህመድ

55

ኢዜአ ህዳር 9 /2012 ብልጽግና የተሰኘው አዲሱ ውህድ ፓርቲ ብልጽግናን በቁስ ብቻ ሳይሆን በሁለንተናዊ አግባብ እንደሚያረጋግጥ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ/ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ በፓርቲው ውህደት ዙሪያ በፌስ ቡክ ገፃቸው መልእክት አስተላልፈዋል።

በዚህም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለሶስት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ በድርጅቱ ውህደት ፣ በአዲሱ ፓርቲ ፕሮግራምና በህገ ደንብ ዙሪያ እንደተወያየ ነው ያነሱት።

ይህን ተከትሎም ስራ አስፈጻሚው በሶስቱም አጀንዳዎች ላይ የሚያግባባና የሚያቀራርብ ሃሳብ ማንጸባረቁን ነው ዶክተር አብይ የገለጹት።

ውህደቱን በተመለከተም የስራ አስፈጻሚው አባላት ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሀሳባቸው  በነፃነት እንዲንሸራሸር በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል ብለዋል።

በዚህም በመጀመሪያ ቀን ውሎ ለየብቻ የነበሩ ፓርቲዎች ተዋህደው የብልፅግና ፓርቲ ተብለው ለመቀጠል መወሰናቸውን ጠቅሰዋል።

ብልጽግና ለኢትዮጵያ በቁስ ብቻ የሚገለጽ አለመሆኑን የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ በክብር፣ በነጻነት አንዲሁም ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የሚችል ፓርቲ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል ብለዋል።

በኢትዮጵያ "አሁን ያለውን የተበታተነ ጉልበት ሰብሰብ አድርጎ በጋራ በመቆምና ያንኑን በመምራት ከግብ ለማድረስ እንድንችል መወሰናችንም ትልቅ ውሳኔ ነበር" ብለዋል።

የውሳኔው እያንዳንዱ እርምጃም ህግን የተከተለ እንዲሆንና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈፀም በማድረግ የተሳካ ውጤት ማምጣት ተችሏልም ብለዋል።

የፌደራል ስርዓቱ በየጊዜው የሚሻሻልና የሚያድግ መሆኑን ያወሱት ዶክተር አብይ፤  እስካሁን የነበሩ ስህተቶችን በሚያርምና የሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋ የሚያከብር፤ እውቅና የሚሰጥ እንዲሁም ሁሉን ባሳተፈና በሚገባቸው ልክ የሚያስፈልጋቸውን ማቅረብ በሚያስችል ማንነት የሚደራጅ ፓርቲ እንዲሆን መወሰኑንም አስታውቀዋል።

በዚህም አግባብ "ፓርቲው ከአማርኛ በተጨማሪ ኦሮሚኛ፣ትግሪኛ፣ ሶማልኛ እና አፋርኛን የፓርቲው የስራ ቋንቋ አድርጎ ከመወሰኑም በላይ እነዚህ ቋንቋዎች የፌዴራል የስራ ቋንቋ እንዲሆኑ ይሰራልም" ነው ያሉት ዶክተር አብይ።

ውህደቱ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለፓርቲው አባላት ታላቅ ድል ስለሆነም  "እንኳን ደስ አላችሁ" በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም