ቀጥታ፡

መንግስት በአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ፈጣንና ትክክለኛ መረጃ ባለመስጠቱ ግጭቶች እየተባባሱ ነው - ተፎካካሪ ፓርቲዎች

ኢዜአ ሕዳር 09 / 202 ዓ.ም.መንግስት በአገሪቷ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ፈጣንና ወቅታዊ መረጃ ለህብረተሰቡ ባለማድረሱ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እንዲባባሱ ማድረጉን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። ፓርቲዎቹ መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበር ዳተኝነት እንዳለበትም ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተፎካካሪ  የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ግጭትና ብጥብጥን ተገን በማድረግ ስልጣን ለመያዝ መሞከር የታሪክ ተጠያቂ እንደሚያደርግም ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት (ኢዴህ) ምክትል ሊቀመንበርና የሀዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ገብሩ በርሄ በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች እንዲባባሱ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ማህበራዊ የትስስር ገፆች ትልቁን ሚና ይጫወታሉ። ሌሎች አገሮች የተፈጸሙ ድርጊቶችን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝ ኢትዮጵያ ወስጥ ተደረገ ብሎ በማህበራዊ ሚዲያ መልቀቅም እየተለመደ መጥቷል ብለዋል። ይህም ግጭቱ እንዲባባስ ማድረጉን ገልጸው፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ሁሉንም ዜጋ ተጎጂ የሚያደርግ በመሆኑም እንዳይባባሱ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ፈከና እንደሚሉት ደግሞ "መንግስት በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚለቀቁ የሀሰት መረጃዎችን መቆጣጣር ባለመቻሉ ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል"። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢዴአን) ሊቀመንበር አቶ ግዑሽ ገብረስላሴ በበኩላቸው   መንግስት የአገሪቷን ሁኔታ አስመልክቶ ወቅታዊና ፈጣን መረጃ እያደረሰ አለመሆኑን ነው የሚገልጹት። ይህም ህብረተሰቡ በፌስቡክና በሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾች በሚያገኘው መረጃ ግጭቶች እንዲባባሱ ከማድረግ ባለፈ ህግም በተደጋጋሚ እንዲጣስ አድርጓል፤ "መንግስትም ህግ የማስከበር ዳተኝነት አሳይቷል" ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ማንኛውም አካል ግጭትና ብጥብጥን ተገን በማድረግም ስልጣን ለመያዝ መሞከር የታሪክ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸውም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል። መንግስትም አሁን በአገሪቷ እየታየ ያለው ህገ-ወጥ ድርጊት እንዲቆም የህግ የበላይነትን ለማስከበር በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ በማሳሰብ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም