ቀጥታ፡

የኢሕአዴግ ውህደት ለዳበረ ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ወሳኝ ነው--- የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች

ህዳር 9/2012 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢሕአዴግ ውህደት ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራላዊ ሥርዓትን ለማጎልበት ወሳኝ እንደሆነ ኢዜአ ያነጋገራቸው የነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። ነዋሪዎቹ እንዳስረዱት ግንባሩ ራሱን ወደ ውሁድ ፓርቲ ለመለወጥ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የአገሪቱን ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍትሐዊ የስልጣን ባለቤትነት ያሳድጋል። በኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች መካከል የነበረውን ልዩነት ወደ አንድ ለማምጣት የተደረሰው ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የ03 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ያሬድ ባሻዬ በሰጡት አስተያየት ውህደቱ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ''ፋይዳው የላቀ'' ነው ይላሉ። ቀደም ሲል በአገሪቱ የነበረውን የፌዴራል ሥርዓት የ''ይስሙላ'' በማለት የገለጹት አስተያየት ሰጪው፣ውህደቱ ትክክለኛና አሳታፊ ሥርዓት በመመስረትና የዜጎችን ፍትሃዊ የስልጣን ባለቤትነት እንደሚያጎለብት ገልጸዋል፡፡ የከተማው 04 ቀበሌ ነዋሪ አቶ አካሉ ሺፈራው በበኩላቸው "ውህደቱ ቀደም ሲል አጋር ድርጅቶች ተብለው የተፈረጁትን ክልሎች ወደ እኩል ተጠቃሚነት በማምጣት ለአገር ዕድገትና ብልጽግና የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያደርጋቸዋል" ብለዋል፡፡ ውህደቱ በአገሪቱ የዳበረ ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን በማስፈንና የሕዝቦችን ፍትሀዊ የስልጣን ባለቤትነት በማረጋገጥ የመብታቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተናገሩት ደግሞ የሕግ ባለሙያው አቶ ባጫ ታፈሰ ናቸው ፡፡ በውህደቱ የህዝቦችን የዘመናት የመብት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ ፓርቲው የተለያዩ የሃገሪቱን ቋንቋዎች ለመጠቀም መወሰኑም በቀጣይ ለሚያደርገው ጉዞው ስኬት አዎንታዊ እገዛ እንደሚኖረው አስረድተዋል። የአገሪቱን ሕዝቦች አንድነት በማጠናከር አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚን ለመገንባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በውህደት ጉዳይ ላይ ያደረገውን ስብሰባ ትናንት አጠናቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም