ቀጥታ፡

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በሰላም እንዲካሄድ ዝግጅት ተደርጓል---የፀጥታ አካላት

ኢዜአ ህዳር 9 / 2012 ዓ.ም የሲዳማ በክልል የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በሰላም እንዲካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን የሲዳማ ዞንና የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ፀጥታ አካላት ገለፁ። የፀጥታ አካላቱ ቅድመ ዝግጅቱን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የሲዳማ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ እንደገለጹት ከሚመለከታቸው አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር በተሰሩ ሥራዎች ለህዝበ ውሳኔው የቅስቀሳና የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ በሰላም ተጠናቋል ፡፡ነገ በሚካሄደው ህዝበ ውሳኔም ህብረተሰቡ ያለምንም ሥጋት ድምጹን እንዲሰጥ፣ በዕለቱም ሆነ ድምፅ ከተሰጠ በኋላ ያለው ሂደት ሠላማዊ እንዲሆን በፀጥታ አካላቱ በኩል በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ለእዚህም ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከደቡብ ክልል ልዩ ኃይልና ከመደበኛ ፖሊስ ጋር ቅንጅት ተፈጥሮ የፀጥታ ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሠላም ማስጠበቅ ተግባሩ የሚሊሻ አባላትና ከ10 ሺህ በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እንደሚሳተፉም አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።እንደ አቶ አለማየሁ ገለጻ የህዝበ ውሳኔውን ሂደት ሰላማዊ ከማድረግ ባለፈ በሃዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን የሚገኙ የተለያዩ አካላትን ደህንነት ለማረጋጥ በቂ ዝግጅት ተደርጓል። በድምጽ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የሚነሱ ቅሬታዎችና የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ካሉ አፋጣኝ ፍትሕ ለማስፈን ጊዜያዊ ተዘዋዋሪ ችሎቶች መዘጋጀታቸውንም ነው የገለጹት፡፡ የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት ሠላማዊነት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ሕብረተሰቡ ትብብር እያደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ካላለቁ የወሰን ጥያቄዎች ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ የነበሩ ቅሬታችን ከአጎራባች ዞኖች ህዝቦች እና የአስተዳደር አካላት ጋር በመወያየት ለመፍታት መሰራቱን ገልጸዋል። "በእዚህም ህዝበ ውሳኔው ከወሰን ማካለል ጋር የሚያያዝ ጉዳይ አለመሆኑ በመተማመን ቅሬታውን ፈተነዋል" ያሉት አቶ አለማየሁ፣ በዕለቱም ችግር እንዳይፈጠር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በህዝበ ውሳኔው ዕለትም ሆነ በኋላ የተከለከሉ ተግባራት መኖራቸውን የተናገሩት አቶ አለማየሁ፣ ህዝበ ውሳኔውን አስመልክቶ መንግስት መግለጫ እስከሚሰጥ ድረስ የሚደረጉ ማናቸውም የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ ሰልፎችና እንቅስቃሴዎች የተከለከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ክልከላውን ተላልፎ በሚደረግ እንቅስቃሴ ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት መደረጉንም አስታውቀዋል፡፡ የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የሠላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ሮዳሞ ኪአ በበኩላቸው የህዝበ ውሳኔው ሂደት በሠላማዊ መንገድ እንዲከናወን ተገቢ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። ህዝቡም ተሳትፎውን ያለከልካይ እንዲያረጋግጥ በዕለቱ ዝግ የሚሆኑ ተቋማት መኖራቸውን አስረድተዋል ፡፡እንደ ኮሎኔል ሮዳሞ ገለፃ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደሩና በሲዳማ ዞኑ የባለሁለት ዕግር ሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ ከዛሬ ማክሰኞ ምሽት 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ አርብ ጠዋት ድረስ ተከልክሏል፡፡ በህዝበ ውሳኔ ዕለትም ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ዝግ ይሆናሉ ፡፡ ገበያዎች በተለይ የጫት ግብይት በሚካሄድባቸው ሥፍራዎች በዕለቱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይካሄድ ኮሎኔል ሮዳሞ አክለው ገልፀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም