ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ አገሪቷን ከችግር ለማውጣት እየተደረገ ባለው ጥረት የሚጠበቅበትን እየተወጣ አይደለም

ህዳር 9/2012 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አገሪቷ ከገባችበት ችግር ለማውጣት በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን ተግባር እያከናወነ አለመሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ። ኮሚሽኑ በበኩሉ የተሰጡትን ተግባራት መወጣት በሚያስችለው የሪፎርም ስራ ላይ መሆኑን ገልጿል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ትናንት ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ የ2012 በጀት ዓመት ዕቅዱን አቅርቧል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹትም ኮሚሽኑ የሚጠቀምበት የማቋቋሚያ አዋጅ 15 ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ ተልእኮውን በአግባቡ ለመወጣት ያዳግተዋል። በዚህ ሳቢያ በተለያዩ ቦታዎች እየተፈጠሩ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሪፖርት ለማድረግና ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ የሚያስችለው ቁመና ላይ አይደለም። በመሆኑም ኮሚሽኑን በአዲስ መልክ ለማዋቀር የሪፎርም ስራዎች በማካሔድ ላይ እንደሆኑ ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኮሚሽኑ የሕዝቡን ብሶት፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣና ሌሎች ችግሮችን ለሚመለከተው አካል ከማቅረብ ይልቅ የዘገዩ እቅዶችን ለምክር ቤቱ ማቅረቡ አግባብ አይደለም ብለዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ፈይሳ በኮሚሽኑ ላይ የተነሳው የውይይት ሃሳብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በግልጽነት እንዲወጣ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። ኮሚሽኑ እያከናወነ ላለው የሪፎርም ስራ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፉን እንደሚያደርግ ገልጸው ኮሚሽኑም በዕቅዱ ውስጥ የሁኔታ ግምገማዎችን በአግባቡ ማስቀመጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል። ያሉበትን ክፍተቶች በማረምና በማስተካከል ሊራመድ እንደሚገባም አክለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም