ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለዋንጫ ለማለፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል

ህዳር 9/2012 በ14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለዋንጫው ለማለፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋሉ። በምድብ አንድ ከተደለደሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ እና መከላከያ ክለቦች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መከላከያ ከምድባቸው አንደኛና ሁለተኛ ሆነው ማለፍ ችለዋል። እንዲሁም ከምድብ ሁለት ተደልድለው ከነበሩት ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ሰበታ ከተማ መካከልም ሰበታ ከተማና ኢትዮጵያ ቡና ወደ ግማሽ ፍጻሜው መግባት ችለዋል። ይህንንም ተከትሎ ሰበታ ከተማ ከመከላከያ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተዋል። በዚህም ሰበታ ከተማ ከመከላከያ ነገ ከቀኑ በ11:00 ሰዓት ወደ ዋንጫው ለማለፍ ይጫወታሉ። የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆኑት የኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም በደጋፊዎቻቸው ህብረ ዜማና በደጋፊዎቻቸው ልዩ የአደጋገፍ ስልት የሚታወቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሐሙስ ከቀኑ በ11:00 ሰዓት ይጫወታሉ። ለዚህ ጨዋታም የስታዲየም መግቢያ ትኬቶች "በአሞሌ ዳሽን ባንክ" ብቻ የሚገኙ በመሆናቸው በእለቱ በየትኛውም የስታዲየም በሮች ትኬን ማግኘት እንደማይቻል የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አንድም የክልል ክለብ ዋንጫውን አንስቶ አያውቅም። ቅዱስ ጊዮርጊስ 5 ጊዜ ዋንጫውን ያነሳ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 4 ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት ችለዋል። እንዲሁም ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ዋንጫውን ሲያነሳ ፈራሹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ 1 ጊዜ ዋንጫውን ማንሳት ችሏል። 14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ይሆናል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም