በአዲሱ በጀት ዓመት ነባር ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ይደረጋል

65
አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 በአዲሱ በጀት ዓመት ከአዳዲሶች ይልቅ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታወቀ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ህብረተሰቡ አዳዲስ የመንገድና ሌሎች መሰረተ-ልማቶች እንደሚጀመሩ ይጠብቃል በዚህ በኩል ቅሬታ አይፈጠርም ወይ ሲሉ? ስጋታቸውን ገልጸዋል። በምክር ቤቱ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2011 ረቂቅ በጀት ላይ ዛሬ የህዝብ ውይይት አካሂዷል። የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ የአገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታና የ2011 በጀት ዓመት የትኩረት ነጥቦች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የአገሪቱ ዕድገት ዘላቂነት እንዲኖረው ከተፈለገና አሁን የተደቀነውን ፈተና ለማለፍ የኢኮኖሚ አወቃቀሩን መቀየር እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥተዋል። እነዚህም ግብርና፣ የወጪ ንግድ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ታክስ ገቢና ሌሎች ላይ መዋቅራዊ ለውጥ ማምጣት ካልተቻለ ኢኮኖሚው እያደገ ሄዶ አንድ ቦታ መቆሙ አይቀርም ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል። ለአብነትም የወጭ ንግድ ላይ በትኩረት መስራት ካልተቻለ የ2011 ረቂቅ በጀትን ተፈጻሚ ለማድረግ እንደሚያስቸግር ነው የገለጹት። የመንግስት የታክስ ገቢን በተመለከተ በ2010 በጀት ዓመት 200 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቢታቀድም ከ150 ቢሊዮን ብር ፈቅ አለማለቱን በመግለጽ በ2011 ታክስ ሰብሳቢ ተቋማት፤ ህብረተሰቡና ሌሎች በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። ዶክተር አብርሃም አገሪቱ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ካብራሩ በኋላ የ2011 በጀት ዓመት ለየት የሚያደርገው ከ2009 እና 2010 የተንከባለሉ የበጀት ጥያቄዎችንም ማስተናገድ የሚጠበቅበት መሆኑ ነው ብለዋል። በበጀት ዓመቱ የፌዴራል መንግስት ለመሰብሰብ ያሰበውን 211 ቢሊዮን ብር ታክስ ማሳካት ካልተቻለ የሚጠየቁ የበጀትና ሌሎች ጥያቄዎችን ማስተናገድ እንደማይቻል ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል። ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች በበጀት ዓመቱ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ዕቅድ አለመያዙን በመጥቀስ ከውጭ በተገኘ ብድር የተወሰኑ የመንገድ ግንባታዎች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል። በረቂቅ በጀቱ ላይ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ዕቅድ ባለመያዙ ህብረተሰቡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ይሰራሉ ተብለው ቃል ተገብቶ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ አያስነሳም ወይ? ሲሉ የምክር ቤት አባላት ጥያቄያቸውን አንስተዋል። ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም የተነሳው ስጋት ትክክል መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ ማስተካከያዎች የሚወሰዱ ከሆነ ለመንግስት ምክረ-ሃሳብ እንደሚቀርብ ገልጸዋል። የሂሳብ ጉድለት፤ የበጀት አስተዳደር፤ በታክስ አሰባሰብ፤ ኮንትሮባንድ፤ የፕሮጀክት አፈጻጸም፤ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በትኩረት ሊሰራባቸው ይገባል ብለው በውይይቱ ላይ የነበሩ ምሁራንና ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ተወካዮች አንስተዋል። ከ2011 ዓመት የ346 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ውስጥ 205 ቢሊዮን ብር ለፌዴራል ካፒታልና መደበኛ በጀት፤ 136 ቢሊዮን ለክልሎች ድጋፍ እና ለዘላቂ ልማት 6 ቢሊዮን ብር ተይዟል። 59 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በአገር ውስጥ ብድር የሚሸፈን የበጀት ጉድለት ነው። ይህም ከ2010 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የፌዴራል ካፒታልና መደበኛ በጀት በ2 ነጥብ 5 በመቶ፤ የፌዴራል መንግስት መደበኛ ወጪ 4 ነጥብ 4 በመቶ፣ የካፒታል በ1 በመቶ ዝቅ ብለዋል። በአንጻሩ ለክልሎች ድጋፍና ለልማት ግቦች ጭማሪ አላቸው። የ2011 ረቂቅ በጀት ከ346 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኖ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲሆን በህዝብ ተወካዮችና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውይይት እየተደረገበት ይገኛል። እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓም ድረስ ይጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም