ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሥራውን ጀመረ

68
ደሴ ኅዳር 8 / 2012 የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ የመማር ማስተማር ሥራውን ጀመረ። ዩኒቨርሲቲው ሥራውን የጀመረው ትናንት ከአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር ከተማሪዎቹ ጋር መግባባት በመደረሱ ነው። የዩኒቨርሲቲ የመካነ ሰላም ካምፓስ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሺበሺ አለባቸው ውሳኔው ከኅዳር 4/2012 ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረው አለመግባባት የተስተጓጎለውን ትምህርት ቀጥሏል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሐሰት መረጃና ወሬ በተማሪዎች መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት መንስዔ ምክንያት መሆናቸውንና በዚህም ስድስት ተማሪዎች ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በተፈጠረው አለመግባባት የውጭ ሃይሎችና ተማሪዎች ዋነኛ ተዋንያን ሆነው መገኘታቸውንና 28 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው ተጣርቶ እንደጥፋት መጠናቸው ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ይወሰዱባቸዋል ብለዋል። የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር የሺወርቅ ላቀው በድርጊቱ የተጠረጠሩ ተማሪዎችንና ግፊት ያደረጉ የውጭ ኃይሎችን ለሕግ በማቅረብ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የሚገኘው ዩኒቨርሲቲ በ2010 ሥራ የጀመረ ሲሆን፣በያዝነው ዓመት ከ4ሺህ 600 ተማሪዎችን መቀበሉን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም