የግብር ድርሻ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የ6 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ ታይቶበታል

108
ህዳር 08/2012 በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተቀመጠው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የግብር ድርሻ የ6 ነጥብ 5 በመቶ ቅናሽ እንደታየበት ጥናት አመለከተ። ሦስተኛው የኢትዮጵያ የግብር ምርምር ጥምረት ዓመታዊ ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ላይ የግብር ድርሻ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 17 ነጥብ 2 በመቶ እንደሚኖረው ግብ ተቀምጧል። በዓመታዊ ስብሰባው ላይ 'የታክስ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ስኬቶችና ተግዳሮቶች' በሚል ርዕስ በቀረበው ጥናታ በአሁኑ ወቅት የግብር ድርሻ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 10 ነጥብ 7 በመቶ ነው። በ2008 ዓ.ም የግብር ድርሻ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት 12 ነጥብ 4 በመቶ የነበረው ሲሆን በተያዘው ዓመት ግን ወደ 9 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጥናቱ አመልክቷል። ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ለግብር ድርሻ መቀነስ ግብርና ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ እንደሌለው በጥናቱ ተገልጿል። እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በ2016 በተካሄደ ትንተና በግብር መሰብሰብና ወቅታዊ አቅም መካከል የ45 በመቶ ክፍተት እንዳለ ጥናቱ አመልክቷል። 40 በመቶ የሚጠጋው ግብር ለመሰብሰብ ያለውን የአቅም ችግር የሚያሳይ መሆኑን ጥናቱ አረጋግጧል። ለግብር መሰብሰብ ተግዳሮት ከተባሉት ውስጥ የሰላምና መረጋጋት እጦት፣ የፍጆታ ወጪ ከአጠቃላይ የአገር ወስጥ ምርት በአንድ በመቶ ዝቅ ማለት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግር እና አዝጋሚ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ተጠቃሽ ናቸው። ህገ ወጥ የገንዘብ ፍሰት፣ ኮንትሮባንድ፣ የፋይናንስ ተቋማት ደካማ ግንኙነት እንዲሁም በግበር ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል ያለው ደካማ የመረጃ ልውውጥ  አና ዝቅተኛ መሰረተ ልማት በጥናቱ እንደ ተግዳቶች ተጠቅሰዋል። በግብር መሰብሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ የላቀ የግብር ማኔጅመንት ስርዓት መዘርጋት፣ የላቀ ትግበራ ቁርጠኝነት፣ የላቀ ስትራቴጂያዊ ሙያዊ አጋርነት፣ የላቀ ተቋማዊ የመፈጸም ችሎታ እና ዘላቂ የግብር ዕድገት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በጥናቱ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል።                                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም