የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋናው ትኩረት ቀሪ ስራዎች ላይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋናው ትኩረት ቀሪ ስራዎች ላይ ነው
ኢዜአ፤ ህዳር 8/2012 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ትኩረት ቀሪ ስራዎች ላይ መሆኑን ተገለጸ። የግድቡ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም 69 ነጥብ 37 በመቶ የሲቪል ምህንድስና ስራው አጠቃላይ 85 በመቶ ያህል መድረሱም ታውቋል። ኢዜአ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደትን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ ተመልክቷል። በምክትል ፕሮጀክት ማናጀር ማዕረግ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሳይት አስተባባሪ ኢንጂነር በላቸው ካሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የግድቡ ስራ በዋነኛነት የዋናው ግድብ፣ የሃይል ማመንጫ ቤቶች (power houses) እና የሃይል ማከፋፈያ ስራዎችን ያካተተ ነው። ለዋናው ግድብ ስራ ከያስፈልገው 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሌት ስምንት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ሙሌት ተከናውኖ የግድቡ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን ገልጸዋል። ዋናው ግድብ ከሚይዘው የውሃ መጠን በላይ ይዞ በሚፈስበት ወቅት የሚቀረውን ውሃ ለማስተናገድ በር የሌለውና በር ያላቸው የውሃ ማስተንፈሻዎች ግንባታ ስራ እየተከተናወነም መሆኑን ገልጸዋል። የውሃ ማስተንፈሻዎቹ ከሚይዙት አቅም በላይ ውሃ ቢመጣ ይህን ማስተናገድ የሚችል የአደጋ ጊዜ የውሃ ማስተንፈሻ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 13 ዩኒቶች ያሉት የሃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ አጠቃላይ የግንባታ አፈጻጸም ከ72 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል። የሃይል ማከፋፈያ የግንባታ ስራው ከ67 በመቶ በላይ እንደጠተጠናቀቀና አጠቃላይ የሲቪል ምህንድስናው ስራው 85 በመቶ ያህል መጠናቀቁን ገልጸዋል። አጠቃላይ የህዳሴ ግድቡን አፈጻጸም 69 ነጥብ 37 በመቶ መድረሱንም አመልክተዋል። የፕሮጀክቱ ዋነኛ ትኩረት በቀሪ ስራዎች ላይ እንደሆነ የገለጹት የሳይት አስተባባሪው፤ ''ትኩረታችን ካለቀው ላይ ሳይሆን ቀሪዎቹ ላይ ነው'' ብለዋል። የሲቪል ምህንድስና ስራ አፈጻጸሙ ላቅ ያለ ቢሆንም የብረታ ብረት ስራ ከ15 ዓመት በመቶ በላይ እና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው 29 በመቶ ያህል ብቻ መከናወኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ለቀሪ ስራዎች ትኩረት በመስጠት በተቀመጠቅ የተቀናጀ የስራ ማጠናቀቂያ ዕቅድ መሰረት ሁሉንም ስራ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ አመልክተዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቆሟል የሚባለው ነገር ትክክለኛ መረጃ ካለማግኘት እንደሆነና የግድቡ ስራ ዕለት ተዕለት በሙሉ አቅም እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። ከሳይት የዘለለ ችግር ሲያጋጥም በፕሮጀክት ቢሮው እንዲፈቱ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል። ''ችግሮቹ ከሳይትና ከፕሮጀክት ቢሮው በላይ ሲሆኑም ለከፍተኛ አመራሮች ቀርበው ውሳኔ እንዲሰጥባቸው የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው'' ብለዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገነባው ከ50 እስከ መቶ ዓመት እንዲያገለግል ታስቦ እንደሆነም አክለዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2015 ዓ.ም ግንባታው ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።