ቀጥታ፡

የጋሸና- ቅዱስ ላሊበላ- ቢልባላ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ መዘግየት ተጽእኖው የጎላ ነው - ነዋሪዎች

ህዳር 8/2012 የጋሸና-ቅዱስ ላሊበላ- ቢልባላን የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ መዘግየት የቱሪስት መዳረሻ በሆነችው የቅዱስ ላሊበላ ከተማ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ። ተቋራጩ በበኩሉ ግንባታው በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ተሰርቶ በሰባት ወራት ጊዜ ይጠናቀቃል ብሏል። የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር የሆነው የቻይና ሬል ዌይ ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን በበኩሉ ግንባታው በአስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ተሰርቶ በሰባት ወራት ጊዜ ይጠናቀቃል ብሏል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ/ በ 1978 ዓ.ም የዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበውን ይሄን ታሪካዊ ስፍራ መጎብኘት የሚያስችል ምቹ የመንገድ መሰረተ ልማት የነዋሪዎች የዘወትር ጥያቄ ነው። የዓለም ቅርስ የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የያዘው የቅዱስ ላሊበላ ከተማ የመንገድ ግንባታ የተጀመረው እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ጥር 2014 ነበር። በኢትዮጵያ መንግስት አንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ብር ተይዞለት በ42 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደነበርም ያስታውሳሉ ነዋሪዎች። ይሁን እንጂ መንገዱ ከአምስት ዓመት በኋላም መጠናቀቅ ባለመቻሉና የነዋሪዎች ጥያቄ ዛሬም ምላሽ ባለማግኘቱ "መንግስት ስማን" እያሉ ነው። የጋሸና-ቅዱስ ላሊበላ- ቢልባላ መንገድ ፕሮጀክት ተጠሪ መሃንዲስ አቶ ደረጄ ዳንዶ በበኩላቸው ግንባታው የዘገየው የመንገዱ የጥራት ደረጃ በማደጉ መሆኑን ይገልጻሉ። ግንባታው ከአስፓልት ወደ አስፓልት ኮንክሪት ደረጃ በማደጉና ለቅርሱ ደህንነት ሲባል የከባድ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ እንዳያልፉ 15 ኪሎ ሜትር ተለዋጭ መንገድ ተጨምሯልም ብለዋል። በዚህም በመጀመሪያው ስምምነት 90 ኪሎ ሜትር የነበረው በተለዋጭ መንገዱ ምክንያት ወደ 105 ኪሎ ሜትር ከፍ እንዲል ተደርጓል፤ በአሁኑ ወቅት ግንባታው 75 በመቶ ተጠናቋልም ብለዋል። ከሚገነቡ መንገዶች ጥራት ጋር በተያያዘም ኅብረተሰቡ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች እንዳሉ ገልጸው፤ ግንባታው በተሻለ የጥራት ደረጃ እንዲከናወን ቁጥጥር እናደርጋለን ብለዋል። የቻይና ሬል ዌይ ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ቁጥር ሶስት ስራ አስኪያጅ ሊ ዊሆንግ በበኩላቸው፤ ደረጃውን የጠበቀ የአስፓልት ኮንክሪት መንገድ እየሰራን ነው ብለዋል። የመንገድ ግንባታውን በጥራት ለማከናወን የድንጋይ መፍጫ፣ የአስፓልት ኮንክሪት ማምረቻ መሳሪያዎችን እንጠቀማለን ብለዋል። ከአስፓልት መንገድ ስራው ጋር በተያያዘም ጥቃቅን ችግሮች ነበሩ፤ አሁን ከኅብረተሰቡ ጋር መልካም ግንኙነት አለን ብለዋል። በመሆኑም ከህብረተሰቡ ጋር እየተነጋገርን በተሻለ የጥራት ደረጃ በሰባት ወራት ውስጥ ሰርተን እናጠናቅቃለን ነው ያሉት። በተጨማሪም ከ 50 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሆነው መንገድ ቀድሞ በመጀመሪያው ስምምነት አስፓልት በመሰራቱ ወደ አስፓልት ኮንክሪት ሲሸጋገር ጥራቱ ከፍ እንደሚል ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ግንባታው ከአስፓልት ወደ አስፓልት ኮንክሪት ደረጃ ሲያድግ ተጨማሪ 400 ሚሊየን ብር መድቧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም