ቀጥታ፡

ለሲዳማ ውሳኔ ሕዝብ ከ2ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ድምፅ ሰጪዎች ተመዘገቡ

ሐዋሳ ኅዳር 8 / 2012ለሲዳማ ውሳኔ ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ለውሳኔ ሕዝብ የሚያገለግሉ የድምፅ መስጫ ቁሳቁስ አቅርቦት በመጠናቀቅ ላይ ነው። የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት በውሳኔ ሕዝቡ  ለመካፈል ድምፅ ሰጪዎች ምዝገባውን አከናውነዋል። ከጥቅምት 27/2011 ጀምሮ የተካሄደው ምዝገባ በመልካም ሁኔታ መጠናቀቁንም አመልክተዋል። ቦርዱ የምዝገባ ሂደቱን በመስክ ጉብኝትና በስልክ የመረጃ ልውውጥ ሲከታተል መቆየቱንም  ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። በዚህም ቦርዱ ባደረጋቸው የመስክ ምልከታዎችና በደረሰው ሪፖርት በምርጫ ጣቢያዎችና በ200 ሜትር ርቀት ውስጥ መገኘት የማይገባቸው የአስተዳደር አካላት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች አካላት የታዩ ሲሆን፣ የተከለከሉ ምልክቶች  ታይተዋል ብለዋል። ለአስፈጻሚዎች የማስተካከያ መልዕክት በማስተላለፍ እርምት መደረጉን አብራርተዋል። ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞና ቀድሞ ግጭት በነበረባቸው የተወሰኑ ቀበሌዎች ከማህበረሰብ ክፍሎች የቀረቡ አቤቱታዎችን ቅኝት መደረጉን ወይዘሪት ብርቱካን ተናግረዋል። ቦርዱ ከፍተኛ የተመዝጋቢ ቁጥር ያለባቸውን ጣቢያዎች በመለየት 175 ጣቢያዎችን በማቋቋም የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን የተቀላጠፈና በታሰበለት ጊዜ ለማጠናቀቅ መታቀዱን ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል። በምዝገባ ሂደቱ የመራጮች ካርድ ወደ ቤታቸው የወሰዱት አንድ አስፈጻሚ ከሥራ እንዲሰናበቱና የመራጮች መዝገብ ይዘው ለመሰወር የሞከሩ ሌላ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን  ተናግረዋል። በተጨማሪም የምዝገባ ሂደቱን ያወኩ አንድ የከተማ አስተዳደር አባል በተጠረጠሩበት የምርጫ ሂደትን የማስተጓጎል ወንጀል በፌዴራል ፖሊስ ምርመራ አንደተደረገባቸው ገልጸዋል። በዞኑና በሐዋሳ ከተማ ለውሳኔ ሕዝቡ የድምጽ መስጫ ቁሳቁስ አቅርቦት እየተጠናቀቀ መሆኑን ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል። ከነገ በስቲያ በሚካሄደው ውሳኔ ሕዝብ በሲዳማ ዞንና በሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና የንግድ ተቋማት ዝግ እንደሚሆኑም ተጠቁሟል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም