በደብረ ብርሐን ከተማ ኢንዱስትሪ ፈቃድ አሰጣጥ የከተማዋን ዕድገትና የህዝቡ ደህንነት ታሳቢ ማድረግ ይገባዋል---የከተማዋ ነዋሪዎች

16
ኢዜአ ህዳር 08 ቀን 2012 ዓ.ም   የደብረ ብርሐን ከተማ የፋብሪካዎች ፈቃድ አሰጣጥ በከተማ ዕድገትና በህዝቡ ደህንነትን ባስጠበቀ መልኩ በጥናት ላይ መመስረት እንደሚገባው ነዋሪዎች ተናገሩ። ዞኑ በበኩሉ ቀደም ሲል በችኮላ ከተሰጡ ፋብሪካዎች በስተቀር አዳዲሶቹ ኢንዱስትሪዎች በከተማዋ ጥናት የተመሰረቱ መሆኑን ገልጿል። ከአዲስ አበባ 130 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሰሜን ሸዋ ዞን ርዕሰ ከተማ ጥንታዊቷ ደብረ ብርሐን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበርካታ ኢንቨስትመንት ማዕከል ሆናለች። ያም ሆኖ በከተማዋ ኢንዱስትሪዎች የሚስፋፉበት መንገድ ግን በከተማዋ ውበትና የትራፊክ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ገጽታ በሚያሳርፍ መልኩ ከዋናው መንገድ ዳር እየተስፋፉ መሆኑን ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ያነሳሉ። ከፋብሪካዎች ተረፈ ምርትና ፍሳሽ ጋር ተያይዞ ለህብረተሰቡ ጤና ጠንቅነት ምክንያት እንደሚሆኑ ስጋታቸውን ተናግረዋል። በደርግ ዘመነ መንግስት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ጸጋዬ አበራ፤ በከተማዋ የሚገኘው የቆዳ ፋብሪካ በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ የጤና ችግር እንዳይፈጥር ከከተማ ወጣ ብሎ እንዲተከል ቢወሰንም መንግስታዊ ስርዓት ሲለወጥ መሃል ከተማ መገንባቱን ያነሳሉ። ዛሬ ድረስ በከተማ የሚተከሉት ኢንዱስትሪዎች የከተማዋን የወደፊት እጣ-ፈንታ ያላገናዘበና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ እንደሆነ ገልጸው፤ የፈቃድ አሰጣጡ ገንዘብ ስለተገኘ ብቻ ሳይሆን በጥናት ላይ መመስረት ይገባዋል ሲሉ ይጠይቃሉ። ሌሎች የደብረ ብርሐን ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አለሙ ዘውዴና ወይዘሮ ድንበሯ ሁሴንም ፋብሪካዎች መንገድ ዳር እየተነገቡ ለከተማዋ ትራፊክ ፍሰትም ሆነ ለጤና ጠንቅ ምክንያት መሆን እንደሌለባቸው ገልጸዋል። የፋብሪካዎች መስፋፋት በስራ ዕድል ፈጠራ የፈጠሩትን ፋይዳ አድንቀው፤ የሚስፋፉበት መንገድ ግን የከተማዋን ዕድገት፣ የህዝቡን ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ መሆን ይገባዋል ነው ያሉት። ለዚህ ደግሞ የሚመከለተው መንግታዊ አካልም ሆነ ባለሃብቶች ጉዳዩን ሊያጤኑት እንደሚገባ ተናግረዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ በድሉ ውብሸት በበኩላቸው፤ ዞኑ በከተማ ዘርፍ ማለትም ለኢንቨስትመንት፣ ለከተማ ቤትና ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱሰትሪዎች የሚሆን መሬት አቅርቦት ረገድ በአማራ ክልል የተሻለ አፈጻጸም ያለው መሆኑን ይናገራሉ። ያም ሆኖ በደብረ ብርሐን ከተማ ቀደም ብለው የተሰጡ ፋብሪካዎች ከዋናው መንገድ የቀረቡ በመሆናቸው ለትራፊክ ፍሰቱም አደጋ የሚያመጡ፣ ለህብረተሰቡም ጤና ጠንቅ እየሆኑ መምጣታቸውን ያምናሉ። ችግሩን ለመፍታት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ አሁን አዳዲስ ኢንዱሰትሪዎች መሬት የሚሰጠው ከከተማ በራቀና በአይነታቸው በኩታ-ገጠም በሚስፋፉበት ስልት ተግበራዊ መሆኑን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም