ኃይማኖች ሰባኪያን፣ መምህራንና ምሁራን ግጭቶችን በትብብር ለመፍታት የሚያስችል ውይይት አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
ኃይማኖች ሰባኪያን፣ መምህራንና ምሁራን ግጭቶችን በትብብር ለመፍታት የሚያስችል ውይይት አደረጉ
ኢዜአ ህዳር 7/2012 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶና የእስልምና ኃይማኖች ሰባኪያን፣ መምህራንና ምሁራን ግጭቶችን በትብብር ለመፍታት የሚያስችል ውይይት አደረጉ። ውይይቶቹ መሬት ላይ ወርደው አንዱ እምነት ለአንዱ ደጀን በመሆን ችግሮችን ለመፍታት እስከ ወረዳ ድረስ ተደራሽ እንደሚሆን አስታውቀዋል። 'የኃይማኖቶች ትብብርና የጋራ መድረክ ለሕዝቦች ሰላምና አንድነት' በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው የውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጴጥሮሳዊያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረትና የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ የተዘጋጀ ነው። ውይይቱን አስመልክተውም የጴጥሮሳዊያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት ሰብሳቢ ቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑና የሙሰሊሞች መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዑስታዝ አቡበከር አህመድ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቷ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ግጭቶች እየተባባሱና ኃይማኖታዊ መልክ እየያዙ በመምጣታቸው፣ ከየትኛውም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ውጭ አማኙ ማኅበረሰብ ውስጥ የማይጠበቁ ጥፋቶች መከሰታቸውን ተከትሎ ግጭቶችን በጋራ ለመፍታት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። ሁለቱ ኃይማኖቶች ከየትኛውም መንግስታዊ ተቋማት በበለጠ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተዕጽኖ የመፍጠር አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑም ለአገር ዘላቂ ሰላምና አንድነት በትብብር መስራት ማስፈለጉን ነው የተናገሩት። መድረኩም ከየትኛውም የኃይማኖትም ሆነ የመንግስት መዋቅራዊ አደረጃጀት የተዘጋጀ ሳይሆን ግጭቱ ያሳሰባቸው ወጣት የቤተ አምነቶቹ ሰባኪያን፣ መምህራንና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተሰሚነት ያላቸው ምሁራን ተነሳሽነት መሆኑንም አብራርተዋል። አገር የጋራ ቤት መሆኗን በመጥቀስም በአንዱ ቤተ አምነት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ሌላው ላይ የሚደርስ ካልሆነ አሳፋሪና ካማንም የማይጠበቅና የትኛውንም ወገን መውጫ ወደሌለው እልቂት የሚከት መሆኑን አንስተዋል። በዚህም ሁለቱ ቤተ እምነቶች ችግሮችን በትብብር በመፍታት፣ የአገር አንድነትና ሰላምን ለማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል። በቤተ እምነቶችና በአማኒያኑ ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ከሁለቱም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ውጭ በሆነ አካሄድ የሚፈጸም በመሆኑ ለመንግስት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች ባሻገር በቅድሚያ እንደሳባኪያንና መምህራን የራስን ሃላፊነት ለመወጣት እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ሃይማኖቶች ለፖለቲከኞች መጠቀሚያ መሆን እንደሌለባቸው በመግለጽ፤ ቤተ አምነቶች አማኞቻቸውን ወደ ፈሪሃ አግዚአብሄር እንዲመለሱና የሃይማኖቶችን አስተምሮ እንዲያከብሩ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል። በየትኛውም የአገሪቷ አካባቢዎች ግጭት ስጋት ሲኖር በመነጋገር መሬት ላይ የወረደ ስራ ለመስራት እስከ ወረዳ ድረስ ተደራሽ የሆነ የጋራ ትብብር መድረኮች እንደሚደረጉም ተናግረዋል።