አገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚወሰዱ የለውጥ እርምጃዎችን እንደሚደግፉ የደሴ ከሚሴና ኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
አገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚወሰዱ የለውጥ እርምጃዎችን እንደሚደግፉ የደሴ ከሚሴና ኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ
ደሴ ሰኔ 13/2010 የጥላቻ ፖለቲካን በይቅርታ በማለፍ አገሪቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት የለውጥ ሥራ እንዲጠናከር የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የደሴ ኮምቦልቻና ከሚሴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ መድረኮች የሚያቀርቧቸውን ህዝባዊ ጥሪ በመቀበል በህዝቦች መካከል አንድነት ለማምጣት የሚደረገው ጥረት ለአገሪቱ አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ተናግረዋል። በደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ ቀበሌ 05 የሚኖሩት አቶ ደምስ አለባቸው ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ጊዜያት የወሰዷቸው የማስተካከያ እርምጃዎች የአገሪቱን የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መምጣቱን ያሳያል፡፡ በህዝቡ ውስጥ ያገባኛል የሚል አገራዊ የኃላፊነት መንፈስ እየተፈጠረ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ ደምስ ብዙሀን መገናኛ የተለያዩ አስተሳሰቦችን ለማስተናገድ የጀመሩት ጥረት እንዲጠናከር ጠይቀዋል ፡፡ የዴሞክራሲ ስርአቱን በአስተማማኝ መሰረት ላይ ማቆም ከተቻለ አገራዊ አንድነት፣ ኢኮኖሚ እድገትና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን በአግባቡ እውን ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ ጥላቻን በማስወገድና ይቅርታ በማድረግ አገራዊ አንድነትና በሕዝቦች መካከል ሕብረት ለመፍጠር የጀመሩት ጥረት እንዲሳካ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ በከሚሴ ከተማ ቀበሌ 05 በጥብቅናና በህግ አማካሪነት የሚሰሩት አቶ አብዱ መሐመድ በበኩላቸው ከምርመራ እስከ ዳኝነት ያለው የተጠርጣሪዎች አያያዝ አገሪቱ ከተቀበለችው ዓለም አቀፍ ህግጋትና ካወጣችው ህገ መንግስት ጋር የማይጣጣምበት ሁኔታ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄን ችግር በመረዳትና ለሀገራዊ ሰላምና አንድነት ሲሉ አለአግባብ ታስረው የነበሩ ወገኖች በይቅርታ እንዲፈቱ ማድረጋቸው አስተማማኝ የፍትህ ስርአት እንዲዘረጋ ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አቶ አብዱ እንዳሉት መልካም አስተዳደርን እንዲሰፍን፣ ህዝብ በመንግስት ላይ ያለው አመኔታ እንዲጠናከርና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር በፍትህ ስርአቱ ላይ የሚስተዋለውን የአፈጻጸም ክፍተት መሙላት ይገባል። "የህግ ባለሙያዎችን ብቃትና የአገለግሎት ዘመን ግምት ውስት ያስገባ ምደባ ሊኖር ይገባልም" ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት ዋጋ እንዳለው ያስተማሩ መሪ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በደሴ ከተማ ሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ንግስት መኮንን ናቸው፡፡ ዶክተር አብይ በተለያዩ ጊዜያት እየወሰዱት ያለው እርምጃ የእርስ በእርስ ጥላቻን ወደ ጎን በመተው መፈቃቀርን የሚያጎለብት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። "ለታራሚ እስረኞች ይቅርታ በማድረግና ግጭቶች በሰከነ አስተሳሰብ እንዲፈቱ አቅጣጫ በመስጠት ንግግራቸውን በተግባር ያሳዩ መሪ ናቸው" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሰላምና አንድነት የጀመሯቸውን ጥረቶች በማገዝ አገራዊ ሰላም እንዲረጋገጥ በተለይ ወጣቱ ታሪካዊ ኃላፊነቱን በመወጣት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ የጥላቻ ፖለቲካ ቀርቶ የህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት የለውጥ ሂደት እውን እንዲሆን የአቅማቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ መጪው ዘመን የተሻለ አገራዊ አንድነት እውን የሚሆንበት፣ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የሚያድግበትና በተለያዩ ምክንያቶች ከአገር የወጡ ዜጎች እውቀታቸውንና ሃብታቸውን ለወገናቸው ጥቅም የሚያውሉበት ዘመን እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡