የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገለጸ
አዜአ ህዳር 7/2012 የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ የዳያስፖራውን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ተሳትፎ ይበለጥ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ኤጀንሲው የመጀመሪያውን ሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ መክሯል። በውይይቱም ዳያስፖራው በአገሩ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ ለማጠናከር የባለድርሻ ሚና ወሳኝ መሆኑ ተመልክቷል። በኤጀንሲው የዳያስፖራ ተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ማስሬ እንደገለጹት፣ በተያዘው ዓመት በርካታ ዳያስፖራዎች በንግድ፣ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዘርፎች የጎላ ተሳትፎ አድርገዋል። በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የጎላ አስተዋጾ እንደነበራቸውም ገልጸዋል። በሩብ ዓመቱ ብቻ ከ1 ሺህ 32 በላይ ዳያስፖራዎች የንግድና ኢንቨስትመንት ፍቃድ መውሰድ ችለዋል። እነዚሁ ዳያስፖራዎች 35 ቢሊየን ብር መነሻ ካፒታል ማስመዝገባቸውንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ከ4 ሺህ በላይ ዳያስፖራዎች የውጭ ምንዛሪ አካውንት በተለያዩ ባንኮች እንዲከፍቱ በማድረግ ከ7 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር በላይ መቆጠባቸውንም አቶ አውላቸው ገልጸዋል። በፋይናንስ ዘርፉ በሰፊው እንዲሳተፍና አገሪቷ እየገጠማት ያለውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ጥረቶች እንዲደረጉ በውይይቱ ተነስቷል። በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳያስፖራው በተለይ በዩኒቨርሲቲ በኩል አስተዋጾ እንዲያደርጉ የተለያዩ ስራዎች ተጀምረዋል። የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ በመንግስትንና በዳያስፖራው መካከል አገናኝ ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል በበቂ የሰው ሃይል መደራጀት አስፈላጊ መሆኑም ተጠቁሟል። በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶችን አቅም በማጠናከር ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ይሰራል ተብሏል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር የዳያስፖራ ማህበራት ተጠሪዎች ዳያስፖራው በአገሩ ኢንቨስት እንዲያደርግና እውቀቱን እንድያጋራ የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። በውይይቱ ላይ የየክልሉ የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች፣ የዳያስፖራ ማህበራትና የባንክ ተወካዮች ተሳትፈዋል። በቴልኖሎጂው ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች፣ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ተወካይና ዓለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት ተወካዮችም ተሳታፊዎች ነበሩ። የኢትዮጵያ የዳያስፖራ ኤጀንሲ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን አገራዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥና መብታቸውን ለማስከበር የተቋቋመ መሆኑ ይታወቃል። ከኤጀንሲው ዋና ዋና ተግባራት መካከልም የዳያስፖራውን መብትና ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ የሚረዱ ስራዎችን ማከናወን ይሆናል። ከዳያስፖራው የሚገኝ የዕውቀት፣ የክህሎትና ቴክኖሎጂ ሽግግርም ኤጀንሲው ትኩረት የሚሰጣቸው አይነተኛ ጉዳዮች ናቸው።