ቀጥታ፡

ህገ ወጥ የቤት ግንባታን ለማስቆም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ

አዜአ  ህዳር 7/2012 በአማራ ክልል በደላሎች አማካኝነት እየተስፋፋ የመጣው ህገ ወጥ የቤት ግንባታ ለማስቆም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም ተጠየቀ። የክልሉ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ከባለድርሻ አካላት ጋር በኮምቦልቻ ከተማ እየተወያየ ነው፡፡ በውይይቱ ወቅት የቢሮው ኃላፊ አቶ ፈንታ ደጀን እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ከ42 ሺህ ቤቶች በላይ ይኖራሉ። ከእነዚህም ማፍረስ የተቻለው ከአንድ ሺህ 500 በታች እንደሆኑ  አመልክተዋል። አብዛኞች ህገ ወጥ ቤቶች የተገነቡትም ባለፉት ሁለት ዓመታት ለውጡን ተከትሎ የመንግስት ስራ በማይኖርባቸው ቀናትና ጨለማን ተገን በማድረግ ነው። የደንብ አስከባሪዎችና ህገ ወጥ ደላሎች በጥቅምና በዝምድና  የሚያመቻቹትን ህገ ወጥ የቤት ግንባታ ለማፍረስ በሚደረገው ጥረት የሰው ህይወት እስከ መጥፋት ጉዳት  እየደረሰ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት ይህን ችግር ለማቃለል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በማህበር ለተደራጁ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እያጣሩ በወቅቱ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ አደራጅቶ ቦታ ለመስጠትም ሃሰተኛ መታወቂያ፣ ከወረዳና ዞን ቤት ያላቸው ዳግም መደራጀትና ሌሎች ችግሮች በስፋት እንደሚስተዋሉ አስረድተዋል። የክልሉ መንግስት ህገ ወጥ ቤቶችን በማፍረስ የህግ የበላይነትን ለማስከበር አሁን ላይ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ ግብረ ኃይል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል። ህብረተሰቡም ህገ ወጥ ደላሎችንና የመሬት ነጋዴዎችን ለመከላከል  ከመግስት ጎን በመቆም የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡ በክልሉ ምክር ቤት የንግድና ኢንዱስትሪ  ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አበራሽ ታደሰ በበኩላቸው ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ህገ ወጦችን ለመከላከል ምክር ቤቱ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል። በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶችን ማፍረስ ፈታኝ ቢሆንም ህግን ለማስከበር ሲባል እንደማይቀር አመልክተው  "ከመገንባቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል ግን ሊቀድም ይገባ ነበር"  ብለዋል፡፡ በከተማቸው ከአንድ ሺህ በላይ በህገ ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች ቢኖሩም ለማፍረስ ያደረጉት ጥረት ፈታኝ እንደሆበባቸው የተናገሩት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከበደ ካሳ ናቸው። ያቋቋሙት ግብረኃይል አጠናክረው የማፍረስ ተግባሩን እንደሚቀጥሉ ጠቁመው ህብረተሰቡ ህገ ወጥነት  ለመከላከል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንዲደግፍ ጠይቀዋል። በምዕራብ ጎጃም ዞን የመርአዊ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮነስትራክሽን ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ  አቶ እንዲህነው  አውደው  ህገ ወጥ የቤት ግንባታን ለመከላከል በየጊዜው ለሚደራጁ ማህበራት ቦታ እየሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት 140 የተደራጁ ማህበራትን ለማስተናገድም 36 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም አመልክተዋል፡፡ ለሁለት ቀን በሚካሄደው ውይይት ከሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ  ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡ በአማራ ክልል ከ650 በላይ ንዑስ፣ ታዳጊ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ከተሞች እንዳሉ ከክልሉ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም