ቀጥታ፡

የላሙ ኮሪደር ባለስልጣን እንዲቋቋም ተጠየቀ

ኢዜአ ህዳር 7/2012  በኢትዮጵያ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን መሀከል የመሰረት ልማት ትስስር እንዲኖር የተጀመረው የላሙ ፕሮጄክት ሂደት ግምገማ በናይሮቢ መካሄዱ ተገልጿል። የቀድሞ የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ የሚመሩት የአፍሪካ ህብረት የመሰረተ ልማት ከፍተኛ ተወካይ ጽህፈት ቤት በጠራው ስብሰባ እንደተገለፀው የላሙ ወደብን ጨምሮ የላሙ ኮሪደርን ለማልማት እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ውጤታማ ነው። በኬንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባደረሰን መግለጫ የላሙ ወደብ የመርከቦች አንድ ማቆያ ግንባታ መጠናቀቁና ከናይሮቢ አዲስ አበባ ያለው የአስፋልት መንገድ ስራ መከናወኑ በአዎንታዊነት ተጠቅሷል። ሶስቱን አገሮች የበለጠ ለማስተሳሰር የመንገድ ፣የባቡር መስመር እና የወደቦች ልማትን የሚያካትተውን ይህን ፕሮጄክት ለማስፈፀም እና ለመከታተል አገሮቹ የጋራ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው እንዲሁም ከአገሮቹ የሚውጣጣና ስራውን የሚመራ አንድ ባለስልጣን እንዲቋቋም ተጠይቋል። ስብሰባው ላይ የተሳተፉት በኬንያ የኢትዮጰያ አምባሳደር መለስ ዓለም የላሙ ፕሮጄክት ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ ትወጣለች ብለዋል። ኢትዮጵያ በመንገድ እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ግንባታ  እያደረገች ያለውን ስራ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል። በላሙ ኮሪደር ላይ የሚነጋገር የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ በያዝነው ዓመት ማብቂያ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም