ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሉት ለመጪዎቹ አስር ዓመታት የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ አዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሉት ለመጪዎቹ አስር ዓመታት የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ አዘጋጀ
ህዳር 6/2012 ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሉት ለመጪዎቹ አስር ዓመታት የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን አስታወቀ። በብሄራዊ የመረጃ ኮሌጅ በደህንነት ጥናት መስክ በዲፕሎማ ደረጃ ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሰልጣኞች ዛሬ ተመርቀዋል። በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሉት ስር በአዲሱ ሪፎርም መሰረት ወደ ኮሌጅ ያደገው ብሄራዊ የመረጃ ኮሌጅ በደህንነት ጥናት መስክ በዲፕሎማ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሰልጣኞችን ነው ዛሬ ያስመረቀው። ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደመለሽ ገብረሚካኤል በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር አገልግሎቱ እያደረገ በሚገኘው ሪፎርም የተለያዩ ተግባራት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡ ለመጪዎቹ አስር ዓመታት የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ የተሰናዳ ሲሆን፤ የአገልግሎቱን ተልእኮና ራዕይ የሚሸከም ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት መጠናቀቁንም ተናግረዋል፡፡ ሰራተኞች መብትና ግዴታዎቻቸውን በማወቅ ተጠቃሚ የሚሆኑባቸው ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል። ሪፎርሙ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ በመሆን ለህዝብና ለሀገር አለኝታነቱን የሚያረጋግጥ ተቋም ለመገንባት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ስራ ለመስራት የሚያስችል አቅም መሆኑንም ጭምር ገልጸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አገልግሎቱ ሀገራዊ ተልዕኮውን ከአለምአቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም ለመወጣት የሚያስችለው ስያሜና ተልዕኮ በአዲስ መልክ ያደራጀ በመሆኑ፤ማቋቋሚያ አዋጁ እንደፀደቀ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ዋና ዳይሬክተር ጀነራሉ አስታውቀዋል፡፡ ተመራቂዎችም የተጠቀሱትን የሪፎም ስራዎች ለማሳካት የሚያስችል የሙያ ስንቅ ማግኘታቸውን ያስታወቁት ኮሚሽነር ደመለሽ፤ ያገኙትን እውቀትና ያዳበሩትን ክህሎት ወደተግባር ሊቀይሩት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አገልግሎቱ በመቶ ቀን እቅዱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በመረጃና ደህንነት ዙሪያ ስልጠና የሚሠጠውን ተቋም ወደ ኮሌጅ ደረጃ ማሳደግ መቻሉን ኮሚሽነሩ ጠቅሰዋል። አክለውም በተቋሙ የሚተገበረው የትምህርት ስርዓት ለሀገር ሰላምና ደህንነት የሚያበረክተውን ፋይዳ ግምት ውስጥ በማስገባት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለማሳደግ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡ ብሄራዊ የመረጃ ኮሌጁ ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ካሳ በበኩላቸው፤ አለም ወደ አንድ መንደር እየመጣች ባለችበት በዚህ ወቅት የሚያጋጥሙ ሀገራዊ የደህንነት ስጋቶችን ለመመከት በደህንነትና መረጃ ጥናት ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ሃይል ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ ብሄራዊ የመረጃ ኮሌጅ በዚህ ረገድ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የእለቱ ተመራቂዎችም የዚህ እቅድ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ኮሌጁ በሀገሪቱ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ወደ ኮሌጅ ለማደግ በሚያደርገው ጥረት የመጀመሪያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ጠንካራ አደረጃጀትና በቂ ሀብት እንዳለው መገንዘባቸውን አስታውሰዋል። አመራሩ ይህን አቅም እንዴት እንጠቀምበት ብሎ በቁርጠኝነት በመነሳት በአጭር ጊዜ ወደ ኮሌጅ ደረጃ እንዲያድግ ያደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑንም አክለዋል። የኮሌጁ ፕሮግራሞች ተገምግመው እውቅና እንደተሰጠው ያብራሩት ዶክተር አንዱዓለም፤ ይህ በአለም አቀፍ ደረጃ ከአቻ ተቋማት ጋር ተባብሮ ለመስራት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የትምህርት አሰጣጡም በጠንካራ ስነምግባር የሚመራ መሆኑን ገልጸው፤በአለም አቀፍ ደረጃ በዘርፉ ጉልህ ሚና የሚያበረክት ተቋም እንዲሆን የከፍተኛ ትምህርትና ጥራት ኤጀንሲ የመደገፍ ሃላፊነትም ግዴታም አለበት ብለዋል፡፡ ዛሬ ለምረቃ የበቁት ሰልጣኞቹ ከብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እንዲሁም ከኢምግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የተወጣጡ ጀማሪና መካከለኛ አመራሮች መሆናቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታውቋል።