ቀጥታ፡

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የድምጽ መስጫ ዕለት ተቋማት እንዲዘጉ ውሳኔ ተላለፈ

ህዳር 6/2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የድምጽ መስጫ ዕለት ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ መወሰኑን አስታወቀ። ምርጫ ቦርዱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በድምጽ መስጫው ዕለት ተቋማት ዝግ እንዲሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር ውሳኔ ተላልፏል። ''የድምጽ መስጫው ዕለት በስራ ቀን መዋሉ በሂደቱ አፈጻጸም ቅልጥፍና ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችል መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት ድምጽ ሰጪዎች በስራ ሰሌዳቸው ምክንያት እንዳይቸገሩና የህዝበ ውሳኔውን ሰላማዊነት ለማስቀጠል በድምጽ መስጫው ዕለት ተቋማት እንዲዘጉ ተወስኗል'' ብሏል። በዚህም መሰረት ሐዋሳ ከተማን ጨምሮ በሲዳማ ዞን ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት በዕለቱ ዝግ ይሆናሉ። ''በመሆኑም በዞኑና በከተማ መስተዳድሩ የሚሰሩ ማናቸውም ተቋማት በምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ 1162/2012 አንቀጽ 161 መሰረት ይህን ውሳኔ ለማስፈጸምና ለመፈጸም የመተባበር ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ከወዲሁ አውቀው ዝግጅት እንዲያደርጉ'' ሲል ቦርዱ አሳስቧል። ቦርዱ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የድምጽ መስጠት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ያስታወቀ ሲሆን የመራጮች ምዝገባ በሁሉም ጣቢያዎች እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም