የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ሆኖባቸዋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በንግድና ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የጸጥታ ሁኔታ ስጋት ሆኖባቸዋል ተባለ
ህዳር 6/2012 ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች በአገር ቤት በንግድና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት ቢኖራቸውም በአገሪቱ እየታየ ያለው አለመረጋጋት ስጋት እንደሆነባቸው ተገለጸ። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሴ የበጀት ዓመቱን የሩብ ዓመት የስራ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የመረጃ ክፍተትና በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው የሠላም መደፍረስ ዲያስፖራው በልማቱ እንዳይሳተፍ እንዳገደው ተገልጿል። የኤጀንሲው ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ ቀላል የመረጃ ክፍተት ትልቅ የሃብት ብክነት እያመጣና በቂ መረጃ ያለመኖርም ስራዎችን ሽባ እያደረገ ነው። ለአብነትም በሌሎች አገራት የሌለና በአሜሪካ ብቻ የተሞከረ የህክምና መሳሪያ ኢትዮጵያዊያን አገር ቤት ለማስገባት ያደረጉት ጥረት በጉምሩክ እና በሌሎችም ተቋማት ፈጥኖ ያለመተባበር ከስድስት ወራት በላይ እንዳጉላላቸው ተናግረዋል። ''ሀሳብን የመግለጽና ከሠላም ተቃራኒ መቆም የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው" ያሉት አቶ መሐመድ ዲያስፖራው በባህልም ሆነ በእሴት ከማይመስለው ማህበረሰብ ጋር እየኖረ መሆኑን አሁን በኢትዮጵያ እየታየ ላለው ችግር እንደ ማስተማሪያ አቅርበዋል። "አገር ቤት ላለው ማህበረሰብ ጥሩ ምሳሌ በመሆን በባህል፣ በእሴት፣ በቀለም ከሚመስላቸው ማህበረሰብ ጋር ተዋህዶና ተከባብሮ ለመኖር ምሳሌነትን ሊያስተምሩ ይገባል" ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደተለያዩ አገራት በመሄድ ከዲያስፖራ አባላት ጋር ተወያይተው ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በርካታ ዲያስፖራዎች ወደ አገር ቤት ገብተዋል። በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የልማት ተሳታፊ ለመሆንም ከአንድ ሺህ በላይ ዲያስፖራዎች የንግድ ፈቃድ አውጥተው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን የኤጀንሲው የተሳትፎ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ማስሬ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሠላም መደፍረስ ተከትሎ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዝ ማሳየታቸውን ጠቁመዋል። በርካታ የዲያስፖራ አባላት በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት ቢኖራቸውም በአንዳንድ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት መዋዕለ-ነዋያቸውን በስራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በሰላም እጦትና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ሳቢያ በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ከኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማግኘት ከታቀደው ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቷን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።