ውህደቱ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለማጎልበት ይረዳል…የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ውህደቱ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ለማጎልበት ይረዳል…የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን
ህዳር 6/2012 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ ለመዋሃድ መወሰኑ ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን መሰረት ባደረገው የሃገሪቱ አንድነት ላይ እየሰራ መሆኑን እንደሚያሳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ፡፡ ውህደቱ የህዝቦችን እኩል የስልጣን ባለቤትነት ለሚያረጋግጥ የፌዴራል ስርዓት መዳበር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ምሁራኑ ተናግረዋል። በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ጸጋዬ ብርሃኑ እንዳሉት ኢህአዴግ ለመዋሃድ መወሰኑ የሚበረታታና በፌዴራል ስርዓቱ ላይ ተደቅኖ የነበረውን የህልውና ስጋትያቃለለ ነው። ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫው እንዳመላከተ ጠቅሰው በሃገሪቱ የሃሳብ የበላይነት እንዲያድግ በር እንደሚከፍትም ጠቅሰዋል። "የድርጅቱን ውህደት አሃዳዊ መንግስት ለመመስረት የሚደረግ ነው" በሚል በአንዳንድ አካላት በሚነሳው አስተያየት እንደማይስማሙም ተናግረዋል። ጥቂት ግለሰቦች የግል ጥቅማቸውን የሚያስጠብቁበትን ስልጣን ለማስቀጠል በመፈለግ ለውህደቱ የተለያየ ስያሜ ሊሰጡ እንደሚችሉም አስረድተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት የፓርቲው ውህደት አሁን ላለው የሃገሪቱ ችግር ብቸኛ መፍትሔ ነው ባይባልም አስተዋጽኦው ግን ቀላል አይደለም። በዩኒቨርሲቲው የፋይናነስ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስስ ኮሌጅ ዲን አቶ ዳባ ገረመው በበኩላቸው እንደተናገሩት ኢህአዴግ ከውህደት በኋላ አሃዳዊ ስርዓትን ያሰፍናል ብለው አያምኑም። አሁን በህዝቡ የሚነሱ የህግ የበላይትን የማስከበር ጉዳዮች ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ መስራት አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል። ከሽግግር መንግስት ጀምሮ ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች እንዳሉ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪው ከውህደቱ በኋላ ፓርቲው አሃዳዊ ስርዓት ሊመሰርት ነው የሚሉ ወገኖች መላምት መነሻው ይኸው ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡