በፍቼ ከተማ ጽዳት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የድርሻችንን እንወጣለን---የከተማዋ ነዋሪዎች

ፍቼ (ኢዜአ) ህዳር 06 ቀን 2012  በፍቼ ከተማ የጽዳት ሥራ የሕብረተሰቡ የዘውትር ተግባርና ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በከተማው የመንግስት ሠራተኞች፣ ነጋዴዎች ወጣቶችና ሴቶች የተሳተፉበት የአንድ ወር የፅዳት ዘመቻ ዛሬ ተጀምሯል።

በጽዳት ዘመቻው በከተማው ልዩ ልዩ ጎዳናዎችና አደባባዮች እንዲሁም የፍሳሽ ማስተላለፊያ ትቦዎች ጠረጋ ተካሂዷል።

ከፅዳት ዘመቻው ተሳታፊዎች መካከል በመንግስት ሥራ የሚተዳደሩት አቶ አየለ መንገሻ በሰጡት አስተያየት ፅዳት ለራስ ጤና ተብሎ በእምነትና በፍቅር የሚከናወን በጎ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪነት ዛሬ የተጀመረው የጽዳት ዘመቻ ቀጣይነት እንዲኖረው የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በከተማው የቀበሌ 04 ሊቀመንበር አቶ ቸሬ ጀቤሳ በበኩላቸው ጽዳት ከቤት እንደሚጀምረ ገልጸው "ጤንነቱ የተጠበቀ ህብረተሰብ ለማፍራት ዘወትር የአካባቢ ጽዳትን መጠበቅ ያስፈልጋል" ብለዋል።

የከተማው ወጣቶች በጽዳት ተግባር ተሰማርተው አካባቢና ከተማቸውን እንዲያፀዱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እንደሚያስትምሩም ቃል ገብተዋል።

የአካባቢ ፅዳት ጥቅሙ የጎላ በመሆኑ የማህበረሰቡ የዘውትር ተግባርና ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የሚጠበቅባቸውን ለማከናወን መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ የከተማው ጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያ ወይዘሮ ይመኙሻል በላይ ናቸው ።

በአካባቢና በከተማ ፅዳት ከመሳተፍ ጀምሮ ድረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ እንዲወገድ ህብረተሰቡን በማስተማር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጽዳት ዘመቻው ዛሬ ጠዋት በፍቼ ከተማ የቆሻሻ ክምችት ባለባቸው አካባቢዎች የተጀመረ ሲሆን በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት አስከ ታህሳስ 05 ቀን 2012 ዓ.ም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የማዘጋጃ ቤቱ የጽዳትና ውበት ተጠሪ አቶ መክብብ ዋለ አስታውቀዋል።

"ወደፊትም ቀጣይነት ያልው የጽዳት ሥራ ለማከናወን የሚረዳ መመሪያ ከህብረተሰቡ ጋር በመነጋገር ለማዘጋጀት ውይይት ይካሄዳል" ብለዋል ።

አቶ መክብብ እንዳሉት በጽዳት ሥራው ከ10 ሺህ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ይሳተፋሉ።

በእዚህም በ36  የውስጥ ለውስጥ መንገዶች፣ በአደባባዮች እና በዋና ዋና መንገዶች ላይ የተጣሉ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች እንደሚነሱ አመልክተዋል።

የፅዳት ዘመቻ ስራውን ያስጀመሩት የከተማው ከንቲባ አቶ ግዛቸው ተረፈ የፍቼ ከተማን ለኑሮ ምቹ፣ ለጤና ተስማሚና ለሥራ ተመራጭ ለማድረግ አስተዳደሩ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከተማዋን አረንጓዴና ፅዱ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከህብረተሰቡ በተጨማሪ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ከንቲባው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም