ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰላም እጦት ሳቢያ ከኢንቨስትመንት ዘርፍ በሩብ ዓመቱ 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቷ ተገለጸ

አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 6 ቀን 2012 በአገሪቱ በሰላም እጦትና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ሳቢያ በተያዘው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወር ከኢንቨስትመንት ዘርፍ ለማግኘት ከታቀደው ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳጣች የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

በአገሪቱ በየጊዜው በሚቀሰቀሰው ግጭትና የሰላም እጦት እንዲሁም በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ሳቢያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን የዕቅዱን ያህል መስራት እንዳልቻለ አስታውቋል።

በሩብ ዓመቱ ከኢንቨስትመንት ዘርፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ማሳካት የቻለው የዕቅዱን 70 በመቶ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሀና አርአያስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለዕቅዱ አለመሳካት ዋናው ምክንያት በየወቅቱ በአገሪቱ የሚቀሰቀሰው ግጭት ነው።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋትና ወደ ግንባታ መግባት፣ የተመቻቻ ፖሊሲና አሰራር መዘርጋት፣ ለቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሻሻልና የባለሃብቶችን ቀልብ ለመሳብ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉ ይታወሳል።

በተለይ በተሰራው የዲፕሎማሲ ስራ በርካታ የውጭ ባለሃብቶች በአገሪቱ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍላጎት ማሳያታቸውን ምክትል ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

''አንዳንዶች ወደ ስራ የሚያስገባቸውን ሂደት ቢጨርሱም በሰላም እጦት ሳቢያ ወደ ስራ የሚገቡበትን ጊዜ ማራዘማቸውን ነግረውናል'' ብለዋል።

ከሐምሌ እስከ መስከረም ድረስ ከተያዘው ዕቅድ አብዛኛውን ለማሳካት የሚያስችሉ አመላካች ነገሮች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

በተለይ በአገሪቱ የተቃውሞ ሰልፍ ሲደረግ የመጀመሪያ ጥቃት የሚደርስባቸው የኢንቨስትመንት ቦታዎች መሆናቸው ደግሞ ለስራው ባለሃብቶችን ስጋት ላይ እንደጣላቸው ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በመንገድ መዘጋት ግብዓቶችን በሚፈለገው ሰዓት ወደ ሚፈለገው ቦታ ባለመድረስ በኢንቨስትመንት ላይ የተመማሩ ባለሃብቶች ከፍተኛ ችግር እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

''የተረጋጋ ሁኔታ በሌለበት ኢንቨስትመንትን ማሳደግ አይቻልም'' የሚሉት ወይዘሮ ሃና፤ የሰላም መደፍረስ ኮሚሽኑን ዕቅዱን እንዳያሳካ እንቅፋት እንደሆነበት አስረድተዋል።

በተጠናቀቀው ሩብ ዓመት በኢንቨስትመንት ዘርፉ 25 ሺህ አዳዲስ የስራ እድሎች ተፈጥረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከዘርፉ ከ4 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማስገባት እቅድ ተይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም