ውህደቱ ኢትዮጵያን "ከሃሰተኛ ፌዴራሊዝም ወደ ትክክለኛው ያሸጋግራታል" - የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ - ኢዜአ አማርኛ
ውህደቱ ኢትዮጵያን "ከሃሰተኛ ፌዴራሊዝም ወደ ትክክለኛው ያሸጋግራታል" - የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ
አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 6 ቀን 2012 የኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች ውህደት ኢትዮጵያን "ከሃሰተኛ ፌዴራሊዝም ወደ ትክክለኛ ያሸጋግራታል" ሲሉ የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ ተናገሩ።
ውህደቱ ሲፈጸም ፓርቲው ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋዎች እንደሚኖሩትም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) የትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስታት በሚመሩ አራት የእህት ድርጅቶች የተዋቀረ ግንባር ነው።
ግንባሩ በአሁኑ ወቅት በውሳኔ ሰጭነት የማይሳተፉ አምስት አጋር ድርጅቶችን አካቶ ይዟል።
አቶ ፍቃዱ ተሰማ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ "ማህበራዊ መሰረታችሁ አርሶ አደር አይደለም" የሚለው ሃሳብ አጋር ድርጅቶች ወደ ግንባሩ እንዳይቀላቀሉ ያደረገ ዋነኛ ምክንያት ነው።
ነገር ግን የግንባሩ እህት ድርጅቶች በሚመሯቸው ክልሎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ቁጥር አጋር ድርጅቶች ከሚመሯቸው ክልሎች እንደሚበልጥም ነው ያመለከቱት።
እንደ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ባሉ ክልሎች ደግሞ በርካታ አርሶ አደሮች እንደiሚኖሩ አክለው፤ ይህም የተጠቀሰው ምክንያት ውሃ እንደማይቋጥር በግልጽ እንደሚያሳይ ነው የተናገሩት።
አሰራሩ አጋር ድርጅቶቹ ባልተሳተፉበት ሁኔታ በእጅ አዙር የኢህአዴግን ውሳኔ እንዲያስፈጽሙ ሲደረግ መቆየቱን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።
በመሆኑም ውህደቱ የእጅ አዙር ጣልቃ ገብነትንና የሞግዚት አስተዳዳርን በማስቀረት ክልሎች ትክክለኛ የፌዴራሊዝም ስርዓትን እንዲተገብሩ ያስችላል ነው ያሉት።
ኢህአዴግ ወደ ውህደት ሲመጣ ከአንድ በላይ የስራ ቋንቋዎችን እንደሚጠቀም ገልጸው፤ ይህም ብዝሃ ልሳን ያላቸውን ዜጎች በመፍጠር ለአገራዊ አንድነት ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
ስኬታማ የፌዴራሊዝም ስርዓት የተገበሩ አገሮች ተሞክሮ ይህን በግልጽ እንደሚያሳይም ጠቁመዋል።
"ፓርቲው ምን ያህል የስራ ቋንቋዎች ይኑሩት" የሚለው ጥያቄ ግን ወደ ፊት በውይይት እንደሚወሰን ጨምረው ገልጸዋል።
የውህደቱ እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ፤ 'ውህደቱን አሃዳዊ ስርዓትን ለመመለስ የሚደረግ ሩጫ' በማስመሰል ህዝብን የሚያደናግሩ አካላት እንዳሉም አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።
በዚህ ስራ ላይ የተጠመዱ አብዛኛዎቹ ከለውጡ በፊት የውህደቱ ግንባር ቀደም አቀንቃኞች እንደነበሩ አስታውሰው፤ "በለውጡ የግል ጥቅማቸው የተነካባቸው አካላት ውህደቱን በሃሰት መረጃ ማጠልሸታቸው የሚጠበቅ ተግባር ነው" ብለዋል።
በኢህአዴግ ውስጥ የውህደት ጉዳይ አዲስ ነገር አለመሆኑ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ተሞክሮ እንደሚያሳይም በአስረጂነት አንስተዋል።
ከ20 በላይ ፓርቲዎች ተዋህደው ደኢህዴንን እንደፈጠሩት ጠቁመው፤ "ድርጅቱ ክልላዊ አንድነትና ብሄራዊ ማንነትን አጣጥሞ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አሳይቷል" ብለዋል።