በጋምቤላ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አንድነትንና ሀገራዊ ለውጡን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አንድነትንና ሀገራዊ ለውጡን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል
ኅዳር 5 ቀን 2012 በጋምቤላ ክልል 14ኛውን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አንድነትንና ሀገራዊ ለውጡን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር የክልሉ ምክር ቤት አስታወቀ። ''ሕገ መንግሥታችን የቃል ኪዳን መሠረታችን ነው!''በሚል መሪ ቃል ከኅዳር 19 ቀን 2012 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በላሬ ወረዳ ኮርገንግ ከተማ ይከበራል። የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ላክደር ላከባክ በዓሉን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በዓሉ የሕዝቦች አንድነትና ለውጡን በሚያጎለብት ሁኔታ ይከበራል። የዘንድሮው በዓል ካለፉት ዓመታት በተለየ የክልሉን ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን በሚያቀራርብና አንድነታቸውን ለማጠናከር ትኩረት ይሰጥበታል ብለዋል። በዓሉ በፓናል ውይይት፣ በሰልፍ ትርዒቶችና ባህላዊ እሴቶች በሚያስተዋውቅ መልኩ በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳዎችና በዞኖች እንደሚከበር አስታውቀዋል። የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት ኅዳር 29 ቀን 2012 በአዲስ አበባ ከተማ ይከበራል። የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት በዓሉን በማስተባበር ተሳትፎ እንደሚያደርግ ይታወቃል።