ሂጅራ ባንክ 527 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወኑን ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
ሂጅራ ባንክ 527 ሚሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ ማከናወኑን ገለፀ
ኢዜአ፤ ህዳር 5/2012 ሂጅራ በሚል ስያሜ በምስረታ ላይ የሚገኘው ከወለድ ነጻ ባንክ ባለፉስ ሶስት ወራት 527 ሚሊዮን ብር የተከፈለ አክሲዮን ሽያጭ ማካሄዱን አስታወቀ። ይህም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የባንክ ምስረታ መስፈርት የሚያሟላ በመሆኑ ሥራውን ለመጀመር ያስችለዋል ተብሏል። ባንኩ አርሶአደሩንና የንግዱ ማህበርሰብን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የባንክ አገልግሎቶችን ለመስጠት በሚያስችል ቁመና በመደራጀት ላይ ያለ መሆኑ ተገልጿል። ባንኩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ባለፉት ሶስት ወራት በተካሄደው እንቀስቃሴ 527 ሚሊዮን ብር የተከፈለ አክሲዮን ሽጧል፤ 1 ነጥብ 04 ቢሊዮን ብር ደግሞ ያልተከፈለ አክሲዮን ሽያጭ አከናውኗል። ይህ የተሸጠው አክሲዮን ከታቀደው እጅግ ከፍተኛ መሆኑም በመግለጫው ተመላክቷል። የባንኩ ስራ አስኪያጅ አቶ ጅብሪል ኡስማን እንዳሉት ባንኩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የባንክ ምስረታ መስፈርት ያሟላ በመሆኑ በሚቀጥለው ታህሳስ ወር ሥራውን በይፋ ለመጀመር እቅድ ተይዟል። ባንኩ ትኩረት አድረጎ የሚሰራው በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች እንደሆነ ነው ስራ አስኪያጁ አቶ ጅብሪል የገለጹት። አክለውም የአክሲዮን ሽያጩ እስከ ህዳር 15 ቀን 2012 ዓም ድረስ የተራዘመ መሆኑንም አስታውቀዋል። ሽያጩ የተራዘመው አክሲዮኑን ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ነው ብለዋል። ባንኩ በአገራዊ ልማት ላይ ከሁሉም አካላት ጋር በትብብር የመስራት ዓላማ እንዳለውም በመግለጫው ተጠቅሷል። አቶ ጅብሪል በመግለጫቸው ባንኩ የያዘው ራእይ ይሳካ ዘንድ ለጀመረው ጥረት ትብብር ላደረጉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት መስጋናቸውን አስተላልፈዋል። በአሁኑ ወቅት አምስት ያህል ከወለድ ነፃ ባንኮች በምስረታ ላይ መሆናቸው ይነገራል። ከእነዚህ መካከል የሆነው ዘምዘም ባንክ ባለፈው ወር በሰጠው መግለጫ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አክሲዮን የሸጠ መሆኑንን አስታውቋል። ከዚህ ውስጥ ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ የሚኾነው የተከፈለ ካፒታል መኾኑን ተጠቅሷል።