ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ገቢዎች ባለስልጣን በሚዛን አማን ከተማ የታክስ ማዕከል ከፈተ

(ኢዜአ) ህዳር 4 / 2012 ኢዜአ የኢትዮጵያ ገቢዎች ባለስልጣን የጅማ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት በሚዛን አማን ከተማ የታክስ ማዕከል ከፈተ። ባለስልጣን   ከአካባቢው የፌደራል ግብር ከፋይ ደንበኞች ጋር ትናንት በሚዛን አማን ከተማ ተወያይቷል። አዲሱ የሚዛን አማን ታክስ ማዕከል ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ በሸካ እና የሸካ አጎራባች በሆኑ የጋምቤላ ዞኖች ለሚገኙ የፌደራል ግብር ከፋዮች አገልግሎት እንደሚሰጥ ተመልክቷል። የኢትዮጵያ ገቢዎች ባለስልጣን የጅማ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ስመኝ ንጉሴ እንዳሉት ከዚህ በፊት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላሉ የፌደራል ግብር ከፋዮች የታክስ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው በጅማ ከተማ ብቻ  ነበር። በአሁኑ ወቅት በአራት ተጨማሪ ከተሞች ላይ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል። "ቀድሞ ሥራ የጀመረው የነቀምት ታክስ ማዕከልን ጨምሮ ሚዛን አማን፣ ጋምቤላና አሶሳ ከተሞች አዲስ የተከፈቱ የታክስ ማዕከላት ናቸው" ብለዋል። አቶ ስመኝ እንዳሉት ማዕከላቱ መከፈታቸው በአካባቢዎቹ የሚገኙ የፌደራል ግብር ከፋዮች በአቅራቢያቸው ፈጣንና ቀልጣፋ የታክስ አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል። ከእዚህ በፊት ግብር ከፋዮች የመንግስት ግብር ለመክፈል እስከ 700 ኪ.ሜ ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰው ይህም ደንበኞችን ለእንግልትና ለከፍተኛ ወጪ ይዳርግ እንደነበር ተናግረዋል። በዞኖቹና አካባቢው ሰፊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚከናወኑባቸውና በርካታ ግብር ከፋዮች ያሉበት በመሆኑ የታክስ ማዕከላቱ ፍትሐዊ የታክስ አሰባሰብን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝም አቶ ስመኝ ጠቁመዋል። የኮሶኮል ጠቅላላ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ፈይሳ በበኩላቸው የታክስ ማዕከሉ በአቅራቢያቸው አገልግሎት መስጠት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።ከዚህ በፊት  የመንግስትን ታክስ ለመክፈል ለበርካታ ዓመታት እስከ ሃዋሳ ከተማ ከ800 ኪ.ሜ በላይ ይጓዙ እንደነበር ገልጸው " በሚዛን አማን ከተማ የታክስ ማዕከል መጀመሩ ጊዜና ወጪ ይቆጥብልናል" ብለዋል። የሕዳሴ አልኮልና ለስላሳ መጠጦች አከፋፋይ ተወካይ አቶ አጥናቸው ውብሸት በበኩላቸው "መንግስት ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት መነሳሳትን ይፈጥራል" ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የታክስ ማዕከሉ በቅርበት መከፈቱ መንግስት ተገቢውን ታክስ በቅርበት ለመሰብሰብ የሚያስችለው መሆኑን ነው የገለጹት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም