አርካይና የመስኖ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እያደረገን ነው... በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
አርካይና የመስኖ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እያደረገን ነው... በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አርሶ አደሮች
ባህርዳር ሰኔ 13/10/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አርካይና መስኖ ፕሮጀክትን ለመስኖ መጠቀማቸው ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በኪንፋዝ በገላ ወረዳ የጠብጠብታ ቀበሌ አርሶ አደሮች ተናገሩ። በአማራ ክልል 15 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ ማልማት የሚያስችሉ 60 የመስኖ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸው ተገልጿል። ጠብጠብታ ወንዝ ላይ በ24 ሚሊዮን ብር ግንባታው በመጠናነቀቅ ላይ ያለው የአርካይና እና መሰል መስኖ ፕሮጀክቶች ተጎብኝቷል። የጠብጠብታ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ገብርዬ ጫቅሌ እንደገለጹት ቀደም ሲል የወንዙን ውሃ በመጠቀም በመስኖ ሲያለሙ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። የወንዙን ውሃ በባህላዊ መንገድ አውጥቶ ለመጠቀም ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ በሚባክነው ውሃ የውሃ እጥረት ይገጥማቸው እንደነበር ገልጸዋል። የዘመናዊ መስኖ ግድብ ግንባታ ሥራ ባይጠናቀቅም ለአገልግሎት በመዋሉ ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ የተሻሻለ የዱቤ ሽንብራ ዘር በዘመናዊ መንገድ ማልማታቸውን ተናግረዋል። በእዚህም ቀደም ያገኙት የነበረው ከሁለት ኩንታል ያነሰ ምርት በአሁኑ ወቅት ከአራት ኩንታል በላይ መድረሱን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ አንዳሉት በቀጣይ ከሽንብራ፣ በቆሎና ሽንኩርት ባለፈ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራ ለመሳተፍ ማህበር በማቋቋም የማንጎ አትክልት ችግኝ እንዲቀርብላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል። "ዘመናዊ የመስኖ ግንባታው ከዚህ ቀደም የውሃ አማራጭ ያልነበረባቸውን ማሳዎች ጭምር ተደራሽ በማድረግ አርሶ አደሩን ከችግር እታደገ ነው" ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ማሬ ጨቅሌ ናቸው። በባህላዊ መስኖ ሲጠቀሙ የነበረባቸውን የውሃ እጥረት፣ ድካምና ልፋት እንዳስቀረላቸው የገለጹት አርሶ አደሩ፣ የመስኖ ፕሮጀክቱ ይበልጥ ውጤታማ እያደረጋቸው መሆኑን አመልክተዋል። በቀጣይም አዳዲስ የሰብልም ሆነ የአትክልት ዝርያዎችን በማልማት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሰሩ የገለጹት አርሶ አደሩ፣ በቀጣይ በማህበር ተደራጅተው በመንቀሳቀስ የመስኖ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያደርጉለት ተናግረዋል። የአማራ ክልል መስኖ፣ ውሃና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ ስንታየሁ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ዘመናዊ የመስኖ ግንባታን ለማስፋፋት በሁሉም አካባቢዎች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የመስኖ ግድቦችን በመገንባት ላይ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ መለሰ እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተገነቡ 564 የዘመናዊ መስኖ ተቋማት 98 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ ለማልማት መቻሉን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 60 የአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ መስኖ ተቋማት እየተገነቡ መሆናቸውን ገልጸው፣ እነዚህም 15 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል። "በግንባታ ላይ ካሉት ውስጥ 9 ሺህ ሄክታር ማልማት የሚችሉት 39 የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች በዚህ በጀት ዓመት መጨረሻ ተጠናቀው ወደ ልማት ይገባሉ" ብለዋል። የአርካይና መስኖ ፕሮጀክትም ከሚጠናቀቁት ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቁመው፣ ፕሮጀክቱ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ ሲገባ 280 ሄክታር ማልማት እንደሚያስችልና ከአንድ ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል። ግንባታውን ያከናወነው የአባይ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጉግሳ መሸሻ በበኩላቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ለዘመናዊ መስኖ ካለው ጥልቅ ፋላጎት የተነሳ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የአካባቢው ነዋሪዎች የለማ ሰብላቸውን ሳይቀር በማንሳት ድጋፍ ማድረጋቸውንም አስረድተዋል። በግንባታ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለመጎብኘት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ የአማራ ክልል የመስኖ፣ ውሃና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ኃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።