ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውሃ ሚንስትሮች በአዲስ አበባ እየተወያዩ ነው

ኅዳር 4 / 2012 በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች ዛሬ በአዲስ አበባ እየመከሩ ነው። ውይይቱ የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በአሜሪካ ጋባዥነት በዋሽንግተን ተገኝተው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የሚካሄድ ነው። ውይይቱ እየተካሄደ ያለው የዓለም ባንክና የአሜሪካ ታዛቢዎች በተገኙበት  መሆኑም ታውቋል። የሚኒስትሮቹ ስብሰባ በግድቡ የውሃ አሞላልና አስተዳደር ላይ ያተኩራልም ነው የተባለው። በውይይቱም የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ፣ የግብፁ የውሃና መስኖ ሚኒስትር ዶክተር ሞሃመድ አብደልና  የሱዳኑ አቻቸው ፕሮፌሰር ያሰር አባስ እየተካፈሉ ይገኛሉ። በአሜሪካ በተካሄደው ውይይት የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ በውሃ ሚኒስትሮች ደረጃ እስከ ጥር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ አራት የቴክኒክ ጉዳይ ውይይቶች ለማካሄድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው የተመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድንም ኢትዮጵያ በናይል ወንዝ ላይ ፍትሃዊና ሚዛናዊ የውሃ አጠቃቀም መብት እንዳላትም ማስገንዘቡ ይታወሳል። ኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኝ ህዝቧን ተደራሽ ለማድረግና ለድህነት ቅነሳ ጥረቷ እንጂ ማንንም አካል የመጉዳት ዓላማ እንደሌላትም አስገንዝባለች። የዛሬው ስብሰባም ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ቀጥለውም በሱዳን ካርቱምና በግብጽ ካይሮ የሚወያዩ ይሆናል ነው የተባለው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም