የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች በኢንቨሰትመንት ለመሰማራት ጥናት እያካሔዱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች በኢንቨሰትመንት ለመሰማራት ጥናት እያካሔዱ ነው
ደሴ ኢዜአ ህዳር 5 ቀን 2012 ዓ.ም......... የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች በኮምቦልቻ ከተማ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችላቸውን አዋጪ ጥናት በማካሄድ ላይ መሆናቸውን በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡሽራ ገለጹ። አምባሳደሩ በሚካሄዱ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ያተኮረ ውይይት ከከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጋር በኮምበልቻ ከተማ ዛሬ ውይይት አካሔደዋል። አምባሳደር አልቡሽራ ባስኑር እንደገለጹት ኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገራት ናቸው። በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶችንም ወደ መካከለኛው ምስራቅ በመላክና ከሃገራቸው የሚመጡ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለመቀበል የሁለቱ አገራት ባለሃብቶች በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው ብለዋል። የአገራቸውን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ በማድረግ በተለይም በኮምቦልቻ ከተማ በጨርቃጨርና በምግብ ነክ ፋብሪካ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የኮምበልቻ ከተማ በመሰረተ ልማት፣ በአመራሩና በህብረተሰቡ የመልማት ፍላጎት፣ ለጅቡቲና ለአሰብ ወደብ ካላት ቅርበት አንፃር በጋራ በመስራት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አረጋግጫለሁ ብለዋል። በመሆኑም የአገራቸው ባለሃብቶች በኮምቦልቻ ከተማ በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ በተደረገው ውይይት መሰረት በአዋጭ ዘርፎች ላይ ጥናት እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል። የኮምቦልቻና ደሴ ከተማ ባለሃብቶችና ነጋዴዎችም ከኢንዶኔዥያ አቻ ከተሞች ጋር በማገናኘት በነጻ ንግድና ግብይት በመሰማራት እንዲጠቀሙ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል ። ይህም የግብርና ምርቶችን፣ የፋብሪካ ውጤቶችንና ጥሬ እቃዎችን በቀላሉ በመለዋወጥ ለሁለቱ አገራት ተጠቃሚነት ድርሻቸው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል። የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ከማል መሃመድ በበኩላቸው የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች በኮምቦልቻ ከተማ በኢንቨስትመንት ቢሰማሩ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ተጠቃሚ ያደርጋሉ ብለዋል። ኮምበልቻ የባቡር ጣቢያ፣ አየር ማረፊያ፣ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በቂ የከርሰ ምድር ውሃ መኖር፣ የህብረተሰቡ የመልማት ፍላጎትና ሰላም ወዳድነት ለኢንቨትመንት ተመራጭ ከተማ ያደርጋታል ሲሉ አብራርተዋል። በዚህም ከ200 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ተሰማርተው በማምረትና ወደ ውጭ በመላክ ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከባለፈው የስራ እንቅስቃሴ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋትም የከተማ አስተዳደሩ አሁን ላይ ከ700 ሄክታር መሬት በላይ መሬት በማዘጋጀት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ጥረት እየተደረገ ነው። የኢንዶኔዥያ ባለሃብቶችም በፈለጉት የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰመራት ለሚያቀርቡት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንደሚያገኙ ለአምባሳደሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የአይጠየፍ አስመጭና ላኪ አክስዮን ማህበር ሥራ አስካሄጅ አቶ አህመድ ሀሰን በበኩላቸው ከኢንዶኔዥያ ባለሃብቶች ጋር በጋራ እንድንሰራ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ተጠቃሚ እያደረገን ነው ብለዋል፡፡ ጥቅምት 2012 ወደ ጃካርታ ከተማ ሂደን ከባለሃብቶች ጋር ለ10 ቀን ያደረግነው የልምድ ልውውጥ ፣ የስራ ባህላቸውንና አገር ወዳድነታቸውን ከመረዳታችንም ባለፈ የጊዜ አጠቃቀማቸውን በመልካም ተሞክሮነት እንድንጋራው አድርጎናል ሲሉ ተናግረዋል ። የተለያዩ የግብርና ምርቶች ላይም እሴት ጨምረን የበለጠ ተጠቃሚ እንድንሆን በር ከፍቶልናል ያሉት አቶ አህመድ የፋብሪካና የግብርና ውጤቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትና ወደ ውጭ ለመላክ ስራ መጀመራቸውን አስረድተዋል ። የመኪና መለዋወጫ፣ የፋብሪካ ግብዓት፣ የግንባታ እቃዎችንና ሌሎች ጥሬ እቃዎችንም ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ከኢንዱንዥያ ጋር ትስስር መፍጠራቸውንተናግረዋል ። አምባሳደሩ የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክንና ለኢንቨስትመንት የሚሆኑ ቦታዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። የኢትዮጵያና የኢንዶኔዥያ ግንኙትን ከ50 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩም መረጃዎች ያመላክታሉ ።