ቀጥታ፡

የሀዲያ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን የተሻለ ገቢ መሰብሰቡን ገለፀ

ሆሳዕና ህዳር 5/2012 ኢዜአ....... የሀድያ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ንኡስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በአንደኛ ሩብ አመት የሰበሰበው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 20 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገለፀ :; ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ እሩብ አመት እቅድ አፈጻጸም በሆሳእና ከተማ ገምግሟል፡፡ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አውላቸው ዮሀንስ እንደገለጹት በሩብ ዓመቱ የተሰበሰበው 185 ሚሊዮን ብር  ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 20 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡ ገቢው ዞኑ ካለው እምቅ አቅምና እቅድ አንጻር ውስንነት የነበረበት መሆኑን የገለጹት ኃላፊዉ በጽህፈት ቤቱ የሰው ኃይል አለመሟላት ፣ በስራው ላይ ያሉ ሰራተኞች ተገቢ ክትትል አለማድረግና ነጋዴው የገቢ ስወራ ማድረግ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ገልጸዋል። በዞኑ ግብርን በወቅቱ በታማኝነት የሚከፍሉ ግብር ከፋዮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው በተቃራኒው የግል ብልጽግናን ባልተገባ መንገድ በሚፈልጉ ነጋዴዎችና ባለሙያዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ተቋሙ በግልና በመንግስት ተቋማት ያለውን የመረጃ ልውውጥ በማዘመን ለግብር አሰባሰቡ እንደ ተግዳሮት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለይቶ ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝም አቶ አውላቸው ተናግረዋል፡፡ የተሻለ የገቢ አፈጻጸም ካላቸው ወረዳዎች አንዱ የሆነው የሌሞ ወረዳ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ንዑስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው አለቃ እንደተናገሩት በጽህፈት ቤቱ የሚከናወኑ ተግባራት ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ በመሆኑ የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመሰጠቱ ህብረተሰቡን ኃላፊነት እንዲሰማው በማድረግ ለውጥ መምጣቱን ገልጸው ይህንን ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ። በበጀት ዓመቱ በዞኑ 747 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ። በመድረኩ ላይ የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች እወቅናና ሽልማት ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም