በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሰብል በዘመቻ እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ሰብል በዘመቻ እየተሰበሰበ ነው
ኅዳር 5 / 2012 በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ከ237ሺህ ሄክታር ላይ የሚገኝን ሰብል ከጉዳት ለመጠበቅ በዘመቻ እየተሰበሰበ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገለጹ። ዋና አስተዳዳሪው አቶ ተክላይ ገብረመድህን ትናንት እንዳስረዱት ሰብሉ እየተሰበሰበ ያለው ከአንበጣና ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ጉዳት ለመከላከል ነው፡፡ በዞኑ በ2011/12 ምርት ዘመን በ119 ሺህ ሄክታር መሬት ያለውን ሰብል በዋነኝነት የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና የክልሉ ጸጥታ ኃይል መሰብሰባቸውን አስረድተዋል፡፡ የኮሌጅና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም በዘመቻው መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀሪውን ሰብል እስከ ኅዳር አጋማሽ ለመሰብሰብ ጥረት እንደሚደረግ አቶ ተክላይ አመልክተዋል፡፡ ሰብላቸው ከተሰበሰበላቸው አርሶ አደሮች መካከል አርሶ አደር አስገዶም ረዳኢ ሠራዊቱና ልዩ ኃይሉ ሰብላቸውን በመሰብሰብ ላከናወኑት ሥራ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ''በአንበጣ መንጋና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሰብሌን ይጎዳል የሚል ፍርሃቴንና ጭንቀቴን ተቃሏል” ያሉት ደግሞ ሰብላቸው የተሰበሰበላቸው አርሶ አደር ፍትዊ በዛብህ ናቸው።