የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ አፈጻጽም 69 ነጥብ 3 ደረሰ

111
ኅዳር 5 / 2012 የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታ  69 ነጥብ 3 መድረሱ ታወቀ። አጠቃላይ የሲቪል ምህንድስና ስራው ደግሞ 85 በመቶ ተጠናቋል ተብሏል። ኢዜአ የግድብ ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃና አጠቃላይ የስራ አንቅስቀቃሴ ተዘዋውሮ ተመልክቷል። የግድቡ ፕሮጀክት ሳይት አስተባባሪ ኢንጂነር በላቸው ካሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የፕሮጀክቱ አካል የሆኑት ዋናው ገድብ፣ ኮርቻ ግድብ፣ ኃይል ማመንጫ ቤቶች፣ የኃይል ማከፋፈያና የውሃ መንደርደሪያ ስራዎችን አካቷል። በዚህም 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 145 ሜትር ከፍታ ያለው ዋናው ግድብ ከሚያስፈልገው 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት ሙሌት ውስጥ 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነው ስራ ተከናውኗል። የኮርቻ ግድብ ግንባታው ከለቀማ ስራዎች በስተቀር 95 በመቶው ተጠናቆ ወደ መጨረሻው መቃረቡን ተናግረዋል። ከግድቡ አቅም በላይ የሚሆን የውሃ ፍሰትን ለማስተናገድ የሚያስችሉ የግድቡ ደህንነት ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በግድቡ መሃል በር አልባ የውሃ ማስተንፈሻ መገንባቱን፣ በግራ ክንፍ ደግሞ ስድስት ማስተንፈሻዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። የውሃ መጠኑ ከዋናው ማስተንፈሻዎች አቅም በላይ ከሆነ ደግሞ የአደጋ ጊዜ ማስተንፈሻ በኮርቻ ግድቡ ግራ ክንፍ ላይ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። የኃይል ማመንጫ ማዕከል (ቤቶች) 13 ዩኒቶች ግንባታ ከ72 በመቶ፣ የኃይል ማከፋፈያ (ዊ-ቻርድ) ስራው ደግሞ 67 በመቶ መድረሱን ኢንጂነር በላቸው ተናግረዋል። በጣሊያኑ ተቋራጭ ሳሊኒ ኢምፐርጂሊ አማካኝነት የሚከናወነው የሲቪል ምህንድስና ስራ 85 በመቶ ደርሷል። የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ይዟቸው የነበሩ የብረታ ብረትና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ለሌሎች የውጭ አገር ተቋራጮች ተሰጥተው አፈጻጸማቸው እንደቅደም ተከተላቸው 15 እና 29 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል። በዚህም በአጠቃላይ የግድብ ፕሮጀክቱ አፈጻጸም 69 ነጥብ 3 በመቶ መድረሱን ነው የሳይት አስተባባሪው የገለጹት። የግድቡ ቀሪ ሁለት ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት ሙሌትና ሲቪል ምህንድና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም የብረታ ብረትና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችን በማፋጠን ግድቡ በተያዘው ጊዜ እንዲጠናቀቅ የጋራ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። ግድቡ በ24 ሰዓት ያለምንም ማቋረጥ በተቀላጠፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም