ቀጥታ፡

ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ትክክለኛና ሚዛናዊ እንዲሆን በአገሪቷ ጠንካራ የሆነ ህግና ስርዓት መስፈን አለበት - ኢዜማ

አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 04/ 2012 ቀጣዩ ምርጫ ነጻ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ አንዲሆን በአአገሪቷ ጠንካራ የሆነ ህግና ስርዓት መስፈን አለበት ሲል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ-ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) አስታወቀ።

ኢዜማ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያና የፓርቲውን እንቅስቃሴ በተመለከተ በአገር ውስጥ ለሚገኙ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በፓርቲው የህገ-ደንብ ትርጉምና ዲሲፕሊን ኮሚቴ ወይዘሮ ሩሃማ ታፈሰ እንደገለጹት ፤ ቀጣዩ ምርጫ ነጻ፣ ትክክለኛና ሚዛናዊ እንዲሆን ጠንካራ የሆነ ህግና ስርዓት መኖር አለበት።

በዚህም በአገሪቷ ግጭቶች እንዲከሰቱ በብሄርና በሃይማኖት ስም ሲሰሩ የቆዩት አካላት ለህግ መቅረብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በወቅታዊ አለመረጋጋቶች ተጠቂ የሆኑትና የተፈናቀሉት ዜጎች ትኩረት ሊያገኙ ይገባል፣ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ቀጣይነት ያለው ውይይት ከባለድርሻ አካላት፣ ከፖለቲከኞችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር መደረግ እንዳለባቸው ኢዜማ አሳስቧል።

ከቀጣዩ ምርጫ በፊት ተቋማዊ የሆነ ወጥነት ያለው አሰራር እንዲኖር በተለይም ከብሄራዊ የምርጫ ቦርድ፣ ከጸጥታና ከፍትህ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አመልክቷል።

በጥቃት የተጎዱትንና የተፈናቀሉትን ዜጎች ፍላጎት ለማሟላት መሰራት እንዳለበትም አሳስበዋል።

የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው፣ ''ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን መንግስት በዋናነት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ የሚገባው በሰላም ማስፈን ላይ ሊሆን ይገባል'' ብለዋል።

''ከዚህ ቀደም በአገሪቷ በተለያዩ ቦታዎች ሲከሰቱ የነበሩት ግጭቶች አስተማሪ እርምጃ ስላልተወሰደባቸው አሁንም በተለያዩ አካባቢዎቸ ችግሮች እየተከሰቱ ናቸው'' ያሉት ሊቀመንበሩ ለዚህም የመንግስት ቸልተኝነት ስለበዛ እንደሆነ አንስተዋል።

''የመንግስትን አቅም ሊገዳደር የሚችል ወይም ከመንግስት አቅም በላይ ነው ብለን የምንወስደው ችግር የለም'' ያሉት አቶ የሺዋስ፣ መንግስት ጉዳዩን በትኩረት አይቶ ቶሎ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ተናግዋል።

በሌላ በኩል ኢዜማ ለሶስት አመት የተዘጋጀ እስትራቴጂክ እቅድ ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚህም ጠንካራ፣ ቀጣይነት ያለውና እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት፣ የህዝቦችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት አመራሮች መገንባት ይገኙበታል።

ፓርቲው ከስድስት ወር በፊት የተመሰረተ ሲሆን ከሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውህደት ማድረጉ ይታወሳል፤ ፓርቲው አሁንም የውህደት ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን በአጠቃላይ በውህደቱ አስር ፓርቲዎች በጋራ እየሰሩ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም