የጋምቤላ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ርክክብ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ርክክብ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ
አዲስ አበባ ኢዜአ ህዳር 04/ 2012 የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀውን የጋምቤላ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ለከተማዋ ከንቲባ አስረከበ።
የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ አቶ ደራር ኩም ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ እጅ መዋቅራዊ ፕላኑን ተረክበዋል፡፡
የጋምቤላ ከተማ መስተዳድር ከዩኒቨርስቲው ጋር በተዋዋለው መሰረት መዋቅራዊ ፕላኑ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ከተቆረቆረች ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረች ሲሆን በተለያዩ ጊዜያት በተዘጋጁ ፕላኖች የከተማው ልማት ሲካሄድ ቆይቷል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ የማስተር ፕላኑ የአገልግሎት ጊዜ በመጠናቀቁ ለከተማው ዕድገት ሲባል ለሁለት ዓመት እንዲራዘም ተደርጎ መቆየቱን የከተማ ከንቲባው አቶ ደራር ኩም በርክክቡ ወቅት ተናግረዋል።
አንድ ከተማ ማልማት የሚቻለው ዘላቂ የሆነ ፕላን ሲኖር በመሆኑ የከተማዋ ዕድገት ተጓትቶ ቆይቷል ይላሉ የከተማዋ ከንቲባ።
የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ኡመድ ኡጫላ በበኩላቸው ከተማዋ ባላት እምቅ ሀብት እና በልማት አውታሮች የበለጸገች መሆኗን ተከትሎ የነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ግጭቶች ሲስተዋሉ ቆይቷል፡፡
በመሆኑም የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን መጠናቀቁ በነዋሪዎች የሚነሱ ግጭቶችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ይቀርፋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ፕላን መምህር አቶ ሞላ የአይኔአበባ እንዳሉት የፕላኑ ጥናት ሲካሄድ ነዋሪዎችን፤ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ባለሙያዎችን እና የሚመለከታቸውን ተቋማት ጭምር ያሳተፈ ነው።
ቀደም ሲል ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታትና ለሌሎች ከተሞች ሞዴል እንዲሆን በርካታ ጥረቶች ተደርጎበታልም ብለዋል አቶ ሞላ።
የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ፤ መዋቅራዊ ፕላኑ ስለተፈጥሮ ሃብት፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባህሪን በመገምገም ሰፊ ጥናት ተደርጎበት ለውጤት በቅቷል ብለዋል፡፡
በአዳማ በተደረገውም አገራዊ የከተሞች ፕላን ላይ ቀርቦም በምርጥ ተሞክሮነት ተመርጧል፡፡
ለሌሎች ከተሞችም ዘላቂ ልማትን ለማስፈን መዋቅራዊ ፕላን አስፈላጊ በመሆኑ ተሞክሮ ሊወስዱ እንደሚገባ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ተናግረዋል።
የከተማዋ ከንቲባም ማስተር ፕላኑን በፍጥነት ወደ ትግበራ በማስገባት የከተማዋ ዕድገት እንዲፋጠን ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡