የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔ በሰላም እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው-ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ - ኢዜአ አማርኛ
የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔ በሰላም እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው-ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ
ሐዋሳ ኅዳር 4 ቀን 2012 በመጪው ሳምንት ለሚካሄደው የሲዳማ ዞን ሕዝበ ውሳኔ በሰላም እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የሐዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ገለጹ። ለሕዝበ ውሳኔው ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ድምፅ ሰጪዎች ተመዝግበዋል። ምክትል ከንቲባው አቶ ጥራቱ በየነ ዛሬ እንደገለጹት በከተማዋ ሕዝበ ውሳኔውን ተከትሎ የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት ኅብረተሰቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው። የሕዝበ ውሳኔው የምርጫ ቅስቀሳ ያለ ችግር እንደተጠናቀቀ ገልጸው፣የመራጮች ምዝገባና የድምጽ አሰጣጥ ሂደቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል። ባለፈው ቅዳሜ በከተማው ምስራቅ ክፍለ ከተማ በሚገኝ አንድ የምርጫ ጣቢያ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በተሽከርካሪ መጥተው ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ሾፌርና አንድ ግለሰብ ከተሽከርካሪው ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ለሕዝበ ውሳኔው ምዝገባ መታወቂያ ካርዳቸው ያልታደሰላቸው ግለሰቦች ችግራቸው ተፈቶ ምዝገባ እንዲያከናውኑ መደረጉንም አስረድተዋል። ለሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት በሐዋሳ ከተማና በሲዳማ ዞን እስካሁን ከ1ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ ለኢዜአ አስታውቀዋል። የሲዳማ ዞን ሕዝብ ከደቡብ ክልል ጋር ለመቆየት አልያም የራሱን ክልል የሚመሰርትበትን ሕዝበ ውሳኔ ኅዳር 10 ቀን 2012 ያደርጋል።