ምክር ቤቱ ሁለት አዋጆችን በአብላጫ ድምጽ ሲያጸድቅ ሁለት አዋጆችን ለዝርዝር እይታ መራ

77
ኢዜአ ህዳር 4/2012፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ማቋቋሚያ አዋጆችን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጆችን በአብላጫ ድምጽ ሲያጸድቅ ሁለት አዋጆችን ለቋሚ ኮሚቴ መርቷል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አራተኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዶ ሁለት አዋጆችን አጽድቆ ቀሪ ሁለት አዋጆችን ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል። ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በዘጠኝ ተቃውሞና በ12 ድምጸ ተአቅቦ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ፤ አዋጅ ቁጥር 1173 እንዲሆን በአብላጫ ድምጽ ወስኗል። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በ10 ተቃውሞና በ10 ድምጸ ተአቅቦ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ፤ አዋጅ ቁጥር 1172 እንዲሆን በአብላጫ ድምጽ ምክር ቤቱ አጽድቋል። በተጨማሪም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፖብሊክ የፌዴራል ድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎችን ክፍፍል ሥርዓትና ተቋማዊ አደረጃጀትን ለመወሰን የወጣውን ረቂቅ አዋጅ እና በጂቡቲና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ቧንቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረገን ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ምርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም