ቀጥታ፡

የአለም የስኳር ህሙማን ቀን ነገ ይከበራል

ኢዜአ ህዳር 3/2012  የስኳር ህሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ተከትሎ ''የስኳር ህመም ቤተሰቤን ይመለከታል'' በሚል መሪ ቃል ነገ በተለያዩ ቦታዎች ነጻ የስኳር ህክምና ምርመራ በመስጠት በዓሉ ይከበራል። የህሙማኑ ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን በሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከል ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን ተናግረዋል። እለቱ ሲከበር ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ግንዛቤ ከመስጠት ባሻገር ነጻ የምርመራ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል። የስኳር ህመም በአለምና በአገራችንም በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ሲሆን ከስኳር ህመም ጋር ከሚኖሩ ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ ይገኛሉ ተብሏል። የአለም አቀፍ የስኳር ህመም ፌዴሬሽን በ2010 ዓ.ም ይፋ ባወጣው መረጃ መሰረት በአለም ላይ 425 ሚሊዮን ሰዎች ከህመሙ ጋር የሚኖሩ ሲሆን በአግባቡ መከላከል ካልተቻለ ቁጥሩ እየጨመረ እንደሚሄድ ስጋት መኖሩንም ነው ወይዘሮ ህይወት ሰለሞን የተናገሩት። በመሆኑም በሽታውን ለመከላከል የአመጋገብ ባህልን ማሻሻል እንደሚገባና በቂ የሆነ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የስኳር ህመም የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ የሚባል እንዳለው ጠቀሰው፤ ''ሁለተኛ ደረጃ የስኳር ህመም አስከፊ ነው'' ብለዋል። ይህንኑ ለመከላከል ከልክ ያለፈ ውፍረትን መቀነስ፤ ሲጋራ ማጨስ ማቆም፣ ለደም ግፊት የሚያጋልጡ ነገሮችን በመቀነስ እራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ስኳር ህመምተኞች ማህበር ፕሬዘዳንት ዶክተር አብዱራዛቅ አህመድ ተናግረዋል። የአለም የስኳር ህመም ቀን  በአገራችን ለ29 ጊዜ ነው የሚከበረው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም