የሰላም እጦት ተጽዕኖ እንዳያሳድር የተማረው ለህብረተሰቡ በተግባር ምሳሌ መሆን እንደሚጠበቅበት ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም እጦት ተጽዕኖ እንዳያሳድር የተማረው ለህብረተሰቡ በተግባር ምሳሌ መሆን እንደሚጠበቅበት ተገለጸ
አዳማ ኢዜአ ህዳር 3/2012፡- የሰላም እጦት በሰውና ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር የተማረው የሰው ኃይል ለህብረተሰቡ በተግባር ምሳሌ መሆን እንደሚጠበቅበት በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ አዳማ ካምፓስ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ መምህራን ገለጹ። መምህራኑ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ አንዳንዳ ካባቢዎች እየተከሰተ ያለው የጸጥታ ችግር የሰው ህይወት ከማጥፋት ሌላ በልማት እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው። ከካምፓሱ መምህራን መካከል አቶ ጌቱ ወዬሳ በሰጡት አስተያየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋምትና በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሠላም እጦት እንደሚስተዋል ተናግረዋል። ችግሩ የመማር ማስተማሩን ሂደት ከመጉዳት ባለፈ በተማሪዎች መካከል ያለውን ሰላማዊ ግንኙነት በማሻከርና በቂ የሆነ እውቀት ሣያገኙ የትምህርት ጊዜያቸው እንዲያልፍ ያደርጋል ፤እያደረገም ነው። አቶ ጌቱ "የህግ አለመከበር ሰዎች በሰላም ወጥተው የማይገቡበት ሁኔታ በመፈጠሩ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም " ብለዋል። በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሰላም ችግር ካለ በሌሎች ቦታዎች ችግር መከሰቱ እንደማይቀር አስረድተዋል። ይህንን አሳሳቢ የሰላም እጦት ችግር በሰውና ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር የተማሩ ሰዎች ለህብረተሰቡ በተግባር ምሳሌ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። እንደ መምህሩ ገለጻ የማህበራዊ ሚዲያውን ትውልዱ እየተጠቀመበት ያለው አካሄድ ለሃገርም ለሕዝብም የሚጠቅም አይደለም። "ይልቁንም አፍራሽ እንቅስቃሴው እያሳደረ ያለው ተጽእኖ አደገኛ በመሆኑ ለበጎ ተግባር ማዋል ከተማረው የሰው ኃይል ይጠበቃል "ብለዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ መምህር ፍጹም ካሳሁን በበኩላቸው በሀገሪቱ እየተከሰተ ያለው የሰላም እጦት ከባድ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም የሰው ህይወት ከማጥፋት ባሻገር የሀገሪቱን ምጣኔ ሀብት እድገትን እየጎዳ መሆኑን ገልጸዋል። በሀገሪቱ የህግ የበላይነት ተከብሮ ሰላም እንዲረጋገጥ ሁሉም አካል ተሳትፎውን መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል። መንግስት ግጭት ከመከሰቱ በፊት የመከላከል አቅሙን ማጠናከር እንዳለበት አመልክተው ህብረተሰቡም ችግሮችን በጥሞና በማጤን የመፍትሄ አካል እንዲሆን ጠቁመዋል። ለዜጎች ደህንነትና ለዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት ሰላም መሰረት እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ ረዳት ሬጂስተርር አቶ አክሊሉ አደራ ናቸው። " ሰሞኑን በአዳማ ከተማ የተከሰተውን የሰላም እጦት ድባብ እንኳን ብንመለከት ከባድ ነው " ያሉት አቶ አክሉሉ ይህም ባለሀብቱ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ ለማልማት ስለሚቸግር ሁሉም በተለይም የተማረው የሰው ኃይል በተግባር አርአያ በመሆን ለሰላም ዘብ እንቁም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።