ቀጥታ፡

122 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ሁለት ኩባንያዎች ወደ ስራ ለመግባት እየተዘጋጁ እንደሆነ ተጠቆመ

ኢዜአ ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም 122 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል የህክምና መሳሪያዎች እና የጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራች ኩባንያዎች ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኢንቨሰትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። የኢትዮጵያ ኢንቨሰትመንት ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሀና አርአያስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በህክምና መሳሪያዎችና በጨርቃጨርቅ ምርት የተሰማሩ ሁለት ኩባንያዎች ወደ ስራ ለመግባት ተዘጋጅተዋል። በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ የህክምና መሳሪያዎች የሚያመርት ኩባንያ በ75 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ስራ ለመጀመር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ እንደሆነ ተናግረዋል። የኩባንያው ወደስራ መግባት የህክምና መሳሪያ ለማስመጣት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚቀንስ ገልጸዋል። በተመሳሳይ በቦሌ ለሚ ምዕራፍ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርክ 'ሻንቴክስ' የተሰኘ የቻይና የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኩባንያ 47 ሚሊዮን ዶላር መዋለ ነዋይ በማፍሰስ ወደ ስራ ለመግባት እየተዘጋጀ እንደሆነ ምክትል ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል። እንደ ወይዘሮ ሀና ገለጻ፤ በፋርማሲቲካል ኢንዱስትሪው ላይ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በተከናወነ ስራ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ኩባንያዎች አሉ። በተያያዘ ምክትል ኮሚሽነሯ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለውን የአገሪቱን ኢንቨስትመንት አዋጅና ደንብ የሚያሻሽል አዲስ ረቂቅ አዋጅ የተዘጋጀ ሲሆን በተያዘው ወር ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል። አዋጁ መሻሻሉ በባለሀብቶች ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን ከመፍታት አንጻር በርካታ ለውጦችን እንደሚያስገኝም ገልጸዋል። የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታውን ማሻሻል፣ በፌዴራልና በክልል ሀላፊዎች መካከል ያለውን የቅንጅት ክፍተት መፍታት፣ የቅሬታ አፈታት ስርዓት ለማሻሻልና ሌሎች ለውጦችን ለማማድረግ አዋጁ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል። ወይዘሮ ሀና እንደገለጹት፤ በነባር አዋጁ ላይ የውጭ ኩባንያዎች ሊሳተፉባቸው የሚችሉባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ባለመካተታቸው ብቻ የውጭ ኩባንያዎቹ ያልተሰማሩባቸው ዘርፎች ነበሩ ። ይህም አገሪቱ ለኢንቨስትመንት ክፍት ያልሆነች አገር ያስመሰለ እንደ ነበር ገልጸው በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ ላይ ቀደም ሲል ያልተካተቱና ለአገሪቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ዘርፎች እንደሚካተቱ ጠቅሰዋል። በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ሩብ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨሰትመንት ለመሳብ መቻሉን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም