ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የወልቂጤን ህዝብ አወያዩ

አዲስ አበባ ሰኔ 13/2010 ወልቂጤ ላይ ህዝቡን ለማወያየት የሄዱት ጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር አብይ አሕመድ እርቅ እንዲወርድ አደረጉ። ባሳለፍነው ሳምንት በወልቂጤ፣ ሶዶና ሀዋሳ ከተሞች ተከስተው በነበረው ግጭት በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በትናንትናው እለት በሀዋሳና በሶዶ ከተሞች በመገኘት ከህዝቡ ጋር ውይይት አድርገዋል። በዛሬው እለትም የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ተዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ከ1 ሺህ 300 በላይ ዜጎች የታደሙበትን የወልቂጤ ከተማ ውይይት አካሄደዋል። በውይይቱም ከተሳታፊዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ለዘላቂ መፍትሔም በሁለቱ ብሔር መካከል የነበረውን ችግር እንድፈቱ ለወጣቶች የቤት ስራ ሰጥተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። በወልቂጤ ከህዝብ ጋር እየተወያዩ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ በከተማውና በአጠቃላይም በደቡብ ክልል በተከሰተው ግጭት ችግሩ ሲፈጠር መከላከል ያልቻሉ የወልቂጤ፣ ሶዶና ሀዋሳ አመራሮችም "ኃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ይለቃሉ ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም